ጅማ ዩኒቨርሲቲ KOFIH ፕሮጀክት 48 የጤና ባለሙያዎችን አሰልጥኖ አስመረቀ፡፡

ሰልጣኞቹ በዩኒቨርሲቲዉ ሴኔት አዳራሽ ተገኝተዉ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ዴቨሎፕመንት ም/ፕሬዝደንት አቶ ኮራ ጡሽኔ ኮሪያ ፋዉንዴሽን ፎር ኢንተርናሽናል ሄልዝ (KOFIH) ላለፉት አምስት አመታት በጅማ ዞን የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናዉን መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
የጤና አገልግሎት ግቦችን ለማሳካት በፕሮጀክቱ የተሰጠዉ ስልጠና ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ያገኘዉን እዉቀት ወደ ተግባር በመቀየር የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ስርዓት ለማሻሻል መትጋት እንዳለባቸዉ አቶ ኮራ ተናግረዋል፡፡
ሰልጣኞቹ ከፕሮጀክቱ የትግበራ ወረዳዎች ከኦሞናዳ፣ ኦሞቤየም፣ ማንቾ እና ዴዶ ጤና ጣቢያዎች የተዉጣጡ ናቸዉ፡፡
ከ48ቱ ተመራቂዎች 15ቱ የአልትራሳዉንድ ስልጣና የተሰጣቸዉ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በአመራር፣ አስተዳደር እና ገቨርናንስ ስልጠና የወሰዱ ናቸዉ፡፡
በስልጠናዉ ሂደት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች የማማከርን የክትትል ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸዉ ተነግሯል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት አዳራሽ በተደረገዉ የምረቃ ፕሮግራም የተለያዩ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን ዉይይት ከተደረገባቸዉ በኋላ ለወደፊት የስራ አቅጣጫ በማስቀመጥ አጠናቀዋል፡፡
ኮሪያ ፋዉንዴሽን ፎር ኢንተርናሽናል ሄልዝ (KOFIH) ላለፉት 5 ዓመታት በጅማ ዞን በተለይም የእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ በስፋት ሲሰራ ቆይቷል፡፡