የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም በጤናው ዘርፍ ለውጥ እያመጣ ነው።

የዋና ዋና ከተሞች የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም አፈፃፀም ሀገራዊ የግምገማ መድረክ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
ፕሮግራሙ በሀገሪቱ ስድስት ዋና ዋና ከተሞች ጅማ፣ አዲስ አበባ፣ ሀረማያ፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ እና መቀሌ እየተተገበረ ያለ ነው።
በግምገማ መድረኩ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እስካሁን ያለው አፈፃፀም መልካም መሆኑን ገልፀው ፕሮግራሙ ዜጎች ሆስፒታል ደርሰው ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ ህይወታቸው እንዳያልፍ የማድረጉን ስራ ያግዛል ብለዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ጅማ ከተማ መልካም ተሞክሮዎች የታዩባቸው መሆናቸው በግምገማ መድረኩ ተገልፅወል።
ይህንን ተሞክሮ በማስፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ደረጃ ከፍ ማድረግ እንደሚገባ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ተናግረዋል።
በግምገማ መድረኩ ጅማ፣ ባህር ዳር፤ ሀዋሳ እና ሀረማያ ዩኒቨርሲቲዎች የሥራ እንቅስቃሴያቸውን አቅርበው ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ ፕሮግራሙን ለመጀመር ዝግጁ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችና ከተሞች ልምድ ያገኙበት እንደሆነ ተጠቁሟል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም ለፖሊሲና ትግበራ ግብዓት የሚሆኑ ምርምሮችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
ለድንገተኛ አደጋ የሚያገለግል አዮ አምቡላንስ፤ የአንድ ማዕከል አምቡላንስ አገልግሎት በማስጀመር ለጅማ እና አካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ተነግሯል።
ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ለአምቡላንስ አገልግሎቱ ከጅማ ከተማ በሶስት የከተማዋ አቅጣጫዎች መሬት እንደተበረከተ ገልፀው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ በጎ አላማ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።