የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ግንዛቤ

ተማሪዎች ከግቢ ዉጪ እንዳይንቀሳቀሱ ተጥሎ የነበረዉ ገደብ ተነሳ፡፡
የኮቪድ-19 ፕሮቶኮሎች ግንዛቤ መፍጠሪያ ዝግጅት በጅማ ዩኒቨርሲቲ አራቱም ካምፓሶች ተካሂዷል።
ዝግጅቱ በጅማ አደጋ ግዜ ክወና ማዕከል አዘጋጅነት “ሁልግዜ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በመጠቀም የኮቪድ-19 መተላለፊያ ሠንሰለትን እበጥሳለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ ተከናዉኗል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ሀብታሙ በዝግጅቱ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ እንደገለፁት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ለበሽታው ተጋላጭ እንዳይሆኑና ተይዘውም ከነበረ ወደ ማህበረሰቡ እንዳያስተላልፉ ለማድረግ ለ10 ቀናት ያህል ከግቢ ሳይወጡ እንዲቆዩ ተድርጉዋል።
ተገድቦ የቆየው የተማሪዎች ከግቢ የመውጣት እንቅስቃሴ ከዛሬ ጀምሮ የተፈቀደ መሆኑን ዶ/ር ታደሠ ሀብታሙ አክለዉ ገልፀዋል።
በጅማ ከተማና ዞን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ግዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በበሽታው የተያዙ ሠዎች ቁጥር 700 ሲሆን 500 ያህሉ ከበሽታው አገግመዋል 17 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።
በጅማ የአደጋ ግዜ ክወና ማዕከል የአደጋ ተጋላጭነት እና ማህበረሰብ ተሳትፎ ሃላፊ ዶ/ር አብዱሰመድ ሁሴን የበሽታው አስጊነት አሁንም በአሳሳቢ ደረጃ ስለሚገኝ ወደ ከፋ ችግር ሳንገባ ከወዲሁ የጥንቃቄ መንገዶችን ሳይዘናጉ ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ም/ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በዳሳ ፈረጃ ተማሪዎች ከግቢ በሚወጡበት ግዜ ለራሳቸውና ለማህበረሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የመጡበትን አላማ ከግብ እንዲያደርሱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ ውስጥ እንደመሆኑ መሰል እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ፣ በማስተባበርና በመምራት የማህበረሰብ አገልግሎቱን በሁሉም ዘርፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተነግሯል።
የኮቪድ-19 ፕሮቶኮሎች ላይ ግንዛቤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ አራቱም ካምፓሶች ለሚገኙ ተማሪዎች እና ሰራተኞች እንዲሁም ለከተማው ማህበረሰብ የተሰጠ ሲሆን በቀጣይም በትምህርት ቤቶችና በጅማ ዞን ደረጃ በስፋት ይከናወናል ተብሏል።