ስርዓተ-ትምህርት ለሀገር እድገት

ስርዓተ-ትምህርት ለሀገር እድገት
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሚያዝያ 7/2013 ዓ.ም
****************************************
ስርዓተ-ትምህርቶች (ካሪኩለም) የሀገሪቱን የልማት ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ መሆን አለባቸዉ፡፡
የተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ ስርዓተ-ትምህርት ላይ የኢንደስትሪ ባለቤቶችን በማሳተፍ ግብዓት ለመሰብሰብ የተዘጋጀ መድረክ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡
የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ገመቺስ ፊሌ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸዉ እንደገለፁት የስርዓተ-ትምህርት ክለሳ እና ግምገማዉ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በኮሌጁ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ስርዓተ-ትምህርቱን ለማሻሻል ግብዓት የሚሰበሰብባቸዉ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ በመክፈቻ ንግግራቸዉ ለአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት በጥራት የተቀረፀ ስርዓተ-ትምህርት የጀርባ አጥንት ነዉ ብለዋል፡፡
“የስርዓተ-ትምህርት ክለሳና ግምገማው እዉቀታችንን ለሀገር ጥቅም የምናዉለበት በመሆኑ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠቃሚ የሆኑ ሀሳቦች የሚፈልቁበት ነዉ” ሲሉ ዶ/ር ጀማል ገልፀዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የጅማ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ስርዓተ-ትምህርት ግምገማ መርሀ-ግብር ማስገባቱ የሚታወቅ ነዉ፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታደሰ ሀብታሙ በበኩላቸዉ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በተመሳሳይ ፕሮግራሞች የየራሳቸዉ ስርዓተ-ትምህርት ስለነበራቸዉ ወጥነት የጎደለዉ አሰራርን ሲከተሉ እንደነበር አስታዉሰዋል፡፡
ም/ፕሬዚደንቱ አክለዉም የግምገማና ክለሳ መድረኩ ከሀገር አልፎ አለማቀፋዊ ደረጃን ያሟላ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
የስርዓተ-ትምህርት ክለሳና ግምገማ ውይይቱ ከዚህ ቀደም በቨርቹዋል ሲዳብር የቆየ ሲሆን ክሬዲት ሀወር፣ ኮመን ኮርስ፣ የፕሮግራም ቆይታ ግዜ፣ የኮርስ ባለቤትነት ጉዳይ የማስተማሪያ ዘዴ፣ኮርስ ኮድ እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አድነዉ ኤርቤሎ እንደተናገሩት የስርዓተ-ትምህርት ክለሳና ግምገማዉ የሀገሪቱን የልማት፣ የኢንደስትሪዉን እና የተመራቂ ተማሪዎችን የመቀጠር ፍላጎት ማሟላትን አላማ ያደረገ በመሆኑ ከዚህ ፕሮግራም የሚጠበቀዉ ዉጤትም አላማዎቹን ከግብ ማድረስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
መድረኩ ነገም የሚቀጥል ሲሆን በዩኒቨርሲቲዎች የሚታየዉን ወጥነት የጎደለዉ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ስርዓተ-ትምህርትን ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል፡፡
በመድረኩ ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታደሰ ሀብታሙ እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡