ስምንት የወላድ እናቶች ማቆያ ማዕከላት ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ሆኑ።

ማዕከላቱ በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ KOFIH ፕሮጀክት እና በጅማ ዞን ጤና ቢሮ ጥምረትና ትብብር በዴዶ፣ ኦሞናዳ፣ ኦሞቤየም እና ማንቾ ወረዳ በተለያዩ ጤና ጣቢያዎች የተገነቡ ናቸው።
የወላድ እናቶች ማቆያ ማዕከላቱን ለመገንባት 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን እንዲሁም አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ከ700 ሺህ ብር በላይ በጥቅሉ ከ 14 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጎዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ በዴዶ ወረዳ ላሎ ቀበሌ ጤና ጣቢያ በተካሄደው የምረቃ ስነ-ስርዓትና ጉብኝት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የKOFIH ፕሮጀክት በእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ የእናቶችና ህፃናት ሞት እንዲሁም ከወሊድ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ችግሮችን በማስቀረት ለማህበረሰቡ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ሀገር በቀል እና አለማቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የሀገሪቱ የጤና አገልግሎት እንዲሻሻልና የህዝቡ ተጠቃሚነት እስኪረጋገጥ በትብብር ከሚሰሩ ተቁዋማት ጋር ያለው ጥምረትና ትስስር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ዴቨሎፕመንት ም/ፕሬዝደንት እና ፕሮጀክቱን በበላይነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ኮራ ጡሹኔ የአንድ ሀገር የጤና አገልግሎት ስኬት ልኬቱ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ህፃናት በጤና ካላደጉ፣ እናቶችም ጤናማ ልጅ ካልወለዱ እና ጤናቸው ካልተጠበቀ የሀገርን እድገት ማሳካት አዳጋች እንደሆነ ተናግረዋል።
በላሎ ጤና ጣቢያ እናቶች ማቆያ ማዕከል በመገልገል ላይ ያሉ እናቶች እንደተናገሩት የአገልግሎቱ መጀመር እንዳስደሰታቸው ተናግረው ማዕከሉ የምግብ፣ የጤና እና መሰል አገልግሎቶች የተሟሉለት መሆኑን ገልፀዋል። ይህም ከዚ በፊት ያጋጥማቸው የነበረውን ውጣ ውረድ እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።
የጅማ ዞን ጤና ቢሮ ተወካይ ወ/ሮ ሙኒራ አባጂሀድ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና KOFIH ፕሮጀክት የተለያዩ የጤና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች፣ ዘመናዊ አምቡላንሶች፣ የአቅም ግንባታ እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ድጋፎችና ስልጠናዎችን በዞኑ ሲያከናውን እንደነበር ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የተደረገባቸው አራቱ ወረዳዎች የትራንስፖርት፣ የአገልግሎት እጠረት፣ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት መስጠት አስቸጋሪ የነበረበት ቢሆንም አሁን ግን የማዕከላቱ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆን የተቀናጀ አገልግሎት መስጠት አስችሏል ብለዋል።
ማህበረሰቡ ደረጃውን የጠበቀ የእናቶች ማቆያ ተገንብቶለት ስለሚገኝ ወሊድን በቤት ወስጥ ማከናወን የለበትም በማለት በማዕከሉ እንዲጠቀሙና ከወሊድ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችን እንዲከላከሉ ወ/ሮ ሙኒራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብም የእውቅና ሠርተፊኬት እና የክብር ሽልማት በማበርከት ደስታውን ገልፅዋል።
እናቶች የማቆያ ማዕከሉን አገልግሎት ለማግኘት በሚሄዱበት ግዜ እንደቤታቸው እንዲሰማቸው ማድረግ ከጤና ባለሙያዎች የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነ ተጠቁሟል።