ለሰው ለሰው የህጻናትና አረጋዊያን መርጃ ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በጅማ ከተማ ለሚገኘው ሰው ለሰው የህጻናትና አረጋዊያን መርጃ ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት ከመምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች በሰበሰበው ሃያ ዘጠኝ ሺ (29፣000) ብር የሚያወጡ የምግብ (5 ኩንታል ጤፍ፤ የጣሳ ዱቄት ወተቶችን) እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በመግዛት ለአረጋዊያም መርጃ ማዕከሉ አስረክቧል፡፡

በስነስርዓቱም ላይ የየኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ የተገኙ ሲሆን፤ በዚህ መልካም ስራ የተሰማሩ ወገኖችን እንዲበረቱ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ነገም ተመሳሳይ ድጋፎች እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

ርክክቡ ሲካሔድ የኮሌጁ ሃላፊዎች፣ መምህራን፣ ሰራተኞች እና የአረጋዊያን መርጃ ማዕከሉ የቦርድ ሰብሳቢ የተገኙ ሲሆን በማጠቃለያውም የአረጋዊያን ማዕከሉን በመጎብኘት ድርጅቱን በዘላቂነት ለመርዳት ቃል በመግባት ተጠናቋል፡፡

ጅማ ዩኒቨርሲቲ፤ በተለያዩ ጊዜያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደገፍ ይታወቃል፡፡ ለሰው ለሰው የህጻናትና አረጋዊያን መርጃ ደግሞ ከዚህ ቀደም በግብርና ኬሌጅ እና በጤና ተቋም ተመሳሳይ ድጋች መደረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡