የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሄዱ፡፡

በዉይይቱ ላይ ከ 3ሺህ በላይ የሚሆኑ የሴኔት፣ የአካዳሚክ፣ አስተዳደር ሰራተኞችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡
መድረኩ የተዘጋጀው በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት የሀገር ሉዓላዊነትንና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ እየሰራ ስለሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለሀገር ሊያበረክት የሚችለዉን አስተዋፅዖ አስመልክቶ ሃሳቦችን ለመለዋወጥና ሙያዊና ቁሳዊ ድጋፎችን ለማሰባሰብ እንደሆነ ተገልፅዋል፡፡ ይኸዉም ቀጥታ የገንዘብና ቁሳዊ ድጋፎችን፣ የህክምና አገልግሎቶችንና አጋዥ ምሁራዊ አስተያየቶችን መለገስን ያካትታል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የህግ ማስከበር ሂደቱን ተከትሎ ለቀረበው ሃገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደተቋም የሚጠበቅበትን አስተዋፅዖ ለማበርከት መወሰኑን ገልፀው “ደማችን ለሀገሩ ክብር ለደማዉ መከላከያ ሰራዊታችን” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የደም ልገሳ ፕሮግራም እንደተጀመረና ሌሎችም ድጋፎችን ዩኒቨርሲቲው እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡
በዚህ ወቅት እንደ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚጠበቀው አስተዋፅዖ ድርብ መሆኑን እና የተቋቋምንለትን አላማ ለማሳካት ሰላም የግድ እንደሆነ፤ ሰላም ከሌለ ደግሞ ተማሪዎች ተምረው ህፃናት አድገው ሃገር ተረካቢ መሆን እንደማይችሉ የገለፁት ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ሰላም መረጋገጡ የግድ እንደሆነና ማህበረሰባችን ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግ የግድ ይላል ብለዋል፡፡
በመድረኩ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት አቶ ከድር አብራሂም ኢትዮጵያዊያን የሀገር ሉዓላዊነት በተነካ ግዜ ይተባበራሉ፣ ይደጋገፋሉ፣ በአብሮነትም ይቆማሉ፤ የዚህ ማሳያ ደግሞ ከፋሺስት ኢጣሊያ ጀምሮ ያለውን የሀገር ጀግንነት ታሪክ እና በነገስታቱ ዘመን የነበረዉን የተማሪዎች ንቅናቄ ለአብነት አንስተዋል፡፡
አቶ ከድር አያይዘውም በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ያደረሰው ቡድን ሀገርን የመምራት እድል የነበረውና በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ ከትጥቅ ትግል አንስቶ ይዞ የመጣውን የግል ጥቅምን የማካበት ፍላጎት በማስቀደሙ የህዝብ ጥያቄ የሆኑትን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የዲሞክራሲ፣ የማንነት፣ የተሳትፎ እና የመልማት ፍላጎትን ችላ ብሎ በህዝብ ግፊት ከስልጣን መዉረዱን አስታውሰዋል፡፡
የህዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ ሳይመልስ ቀርቶ በህዝብ ግፊት ከስልጣን የወረደው ቡድን የለውጡን ሃይል ስራዎች ግብ እንዳይመቱ የማደናቀፍ ስራን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ይህ ሴራም ዛሬ ላይ የሃገር ህልዉናና ሉዓላዊነት ላይ አደጋ ጋርጧል ሲሉ አቶ ከድር ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አባላት በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተቃጣው ጥቃት እኩይ ተግባር በመሆኑ እንደሚያወግዙት፣ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር ርምጃ እንደሚደግፉና ሀገራቸው የምትጠብቅባቸውን አስተዋፅዖ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡ ሴት የዩኒቨርሲቲው አባላት እንደተናገሩት መከላከያ ሰራዊቱ ባለበት አካባቢ ተጉዘንም ቢሆን ድጋፍ ለማድረግና ስንቅ የማቀበል ስራ ለመስራትም ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አባላት ለሀገር ጥሪ ምላሽ የገንዘብ የእውቀትና የጉልበት ድጋፍ እንዲሁም የደም ልገሳ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ አስተያየት ከሰጡት መካከል አንድ የፌዴራል ፖሊስ ተወካይ እንዳሉት የጥፋት ቡድኑ በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት እንዳሳዘናቸው ገልፀው የሃገር ህልውናን ለማስከበርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እስከ ህይወት መስዕዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በመግለፅ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከመንግስት ጎን እንዲሰለፉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የአገራችንን ሉአላዊነት ለማስከበር በተባበረ ድምጽ ላሳዩት ቀርጠኝነት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው የሚበረከቱ የገንዘብ ቁሳዊና ሌሎችም ድጋፎችን በጥቂት ቀናት ውስጥ በማሰባሰብ መንግስት የተያያዘውን ህግ የማስከበር ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቅ እገዛ ለማድረግ እንደሚውል አስገንዝበዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች መካከል በተደረገው ውይይት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ እና ከመንግስት ጎን በመሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በመግለፅ ባለ 5 ነጥብ የጋራ አቋም በመያዝ አጠናቀዋል፡፡