አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለሀገር እድገት

የሃገር ሁለንተናዊ እድገትን ለማፋጠን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን መጠቀምና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተነገረ፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል በትብብር መስራት የሚያስችላቸዉን የመግባቢያ ሰነድ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና ተፈራርመዋል፡፡

ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የዩኒቨርሲቲዉን አብይ የትኩረት አቅጣጫ የሆኑት መማር ማስተማር፣ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎትን ለማሳካት እጅጉን እንደሚያስፈልግ ገልፀዉ፤ ዩኒቨርሲቲዉ በሀገር ዉስጥ እና በዉጭ ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዉ ባለሙያዎች ዲዛይን የተደረጉ ሶፍትዌሮች በሙሉ አገልግሎት እየሰጡ በመሆናቸዉ ዩኒቨርሲቲዉ ወረቀት አልባ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት ወደሚያስችለዉ ደረጃ በመሸጋገር ላይ እንደሚገኝና የሁለቱ ተቋማት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ አድጎ ለሀገር እድገት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ገልፀዋል፡፡

የአለማችን ሀገራት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ የጤና፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ ፋይናንስ እና ሌሎች የስራ መስኮችን ማዘመንና ዉጤማ ማድረግ መቻላቸዉን በርካታ መዛግብት ያሳያሉ፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ዴቨሎፕመንት ም/ፕሬዚደንት አቶ ኮራ ጡሹኔ አለም በቴክኖሎጂ አማካኝነት በፍጥነት እየተለወጠ ስለሚገኝ ከዚህ ተለዋዋጭ ባህሪ ጋር ራስን አስማምቶ መጓዝ ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰዉ፤ ‹‹መማር ማለት መከተል ማለት ሳይሆን መምራት ማለት ነዉ ስለዚህ በፍጥነት በመማርና የፈጠራ ስራዎቸችን በማስፋፋት የአለማችንን የቴክኖሎጂ ሰርዓተ-ምህዳር መቀላቀል ይኖርብናል ብለዋል»፡፡
አቶ ኮራ አክለዉም ለትብብር ስራዉ ግብዓት የሚሆኑ በርካታ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስለሚገኙ ትብብሩ ዉጤታማ እንደሚሆን ያላቸዉን እምነት ተናግረዋል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የተለያዩ የፈጠራ ባለሙያዎች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ የሰሯቸዉን የፈጠራ ስራዎችና ያስገኙትን ጥቅም ያቀረቡ ሲሆን ማዕከሉም እነዚህን ስራዎች ወደ ምርት እንዲገቡ በማድረጉ በኩል እገዛ እንደሚያደርግ ከስምምነት መደረሱ ታዉቋል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና አስታዉሰዉ፤ ስራዉም የሰዉ ልጆች አገልግሎት አሰጣጥን ብቁና ተደራሽ በማድረግ የሚስተዋለዉን ተደራራቢ ጫና ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢንጂነሩ እንዳሉት የትብብር ስራዉ ዉጤት የሚለካዉ የመግባቢያ ሰነድ በመፈርም ሳይሆን ስራዉ ወደ መሬት ወርዶ ለህብረተሰቡ ብሎም ለሀገር እድገት በሚያበረክተዉ አስተዋጽዖ እንደሆነና ለዚህም ስኬት በትጋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና የተመራ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ኤክስፐርቶችና ባለሙያዎች ቡድን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በጅማ ዩኒቨርሲቲ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ ጉብኝት አድረገዋል፡