ማህበረሰብ አገልግሎት በተግባር!

ማህበረሰብ አገልግሎት በተግባር!
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 19/2013 ዓ.ም
**************************************
የዩኒቨርሲቲያችንን ምሁራን፣ ሰራተኞች፣ ተማሪዎች እና ተባባሪ አካላትን በማስተባበር ሰዉ ለ ሰዉ አረጋዊያን መርጃ ማዕከልን ለማጠናከር እንሰራለን፤ ዶ/ር መሀመድ መጫ የጤና ኢንስቲትዩት ም/ፕሬዚደንት፡፡
ኢንስቲትዩቱ በጅማ አደጋ ክወና ማዕከል በኩል ከ135 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸዉ ፍራሾችን ለአረጋዊያንና ህፃናት መርጃ ማዕከሉ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የሰዉ ለ ሰዉ አረጋዊያንና ህፃናት መርጃ ማዕከል መስራችና ሃላፊ ሲስተር ዘመናይ ፍራሾቹን ከደ/ር መሀመድ መጫ እጅ ተረክበዋል፡፡
ዶ/ር መሀመድ መጫ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲዉ ከገንዘብና ንብረት በላይ ያሉትን እወቀቶች በማስተሳሰር ማዕከሉን ለመርዳት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ይህንን ማህበራዊ ሀላፊነት እንደ ተቋምም እንደ ግለሰብም ሞዴል መሆን ስላለብን የዛሬዉን ድጋፍ አድርገናል ያሉት ዶ/ር መሀመድ ስራዉ በምድርም ሆነ በሰማይ ተወዳጅ በመሆኑ በዘላቂነት ፕሮጀክት ቀርፀን የምንሄድበት ነዉ በማለት ገልፀዋል፡፡
ከርክክቡ በኋላም በማዕከሉ ጉብኝት ተደርጓል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሌሎች ኮሌጆችም በሞያ፡ በማህበረሰብ አገልግሎትና በልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ማዕከሉን በተደራጀና በቋሚነት እየደገፉ የሚገኙ ሲሆን ባሳለፍነዉ ሳምንትም ዩኒቨርሲቲው ከ700 በላይ የዘይት ጀሪካኖችን ጨምሮ ድጋፎችን ለማዕከሉ ማበርከቱ ተነግሯል፡፡
የተደረገላቸዉን ድጋፍ አስመልክቶ ሀሳባቸዉን የሰጡት የሰዉ ለ ሰዉ አረጋዊያንና ህፃናት መርጃ ማዕከል ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘመናይ ለዩኒቨርሲቲዉ ምስጋናቸዉን ቸረዉ ማዕከሉ የሚረዳቸዉ የሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ መሰል ድጋፎች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ማዕከሉ በአሁኑ በርካታ የአካል፣ የአዕምሮና ሌሎች እክሎች ያሉባቸዉ ህፃናትና አረጋዊያንን በማዕከሉ በማኖርና በየቤታቸዉ በመርዳት ላይ እንደሚገኝም ሲስተር ዘመናይ ገልፀዋል፡