ሙያዊ ስነ-ምግባር ስልጠና

ሙያዊ ስነ-ምግባር ስልጠና
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 12/2013ዓ.ም
***************************
የተሰጣቸዉ የሙያ ስነ-ምግባር ስልጠና ስራቸዉን በእዉቀት እንዲመሩ እንደሚያስችላቸዉ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ጀማሪ የግዢ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡
ለአምስት ቀናት ሲሰጥ የነበረዉ በግዢ ሙያ ስነ-ምግባርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስልጠና ተጠናቋል፡፡
ስልጠናዉ ለ21 ጀማሪ የግዢ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት ነዉ፡፡
በስልጠናዉ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ እንደተናገሩት መሰል ሙያዊ ስልጠናዎች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዉ ሰልጣኞች የቀሰሙትን እዉቀት በተግባር በማሳየት በግዢ ስራ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በእዉቀት ታግዞ በማስተካከል ለሌሎች ባልደረቦቻቸዉም ማጋራት እንዳለባቸዉ አሳስበዋል፡፡
አትክልት ዉሃ ካልጠጣ እና ካልተኮተኮተ ይቀጭጫል፤ ስልጠናም ለሰዉ ልጆች እንዲሁ ነዉ ያሉት ም/ፕሬዚደንቱ በቀጣይነት የአጭር እና የረጅም ግዜ ስልጠናዎችን ለሰራተኛዉ በማመቻቸት የሰዉ ሃብት ልማትን በማረጋገጥ የዩኒቨርሲቲዉን አለማቀፋዊነት ከስኬት ለማድረስ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ላለፉት አምስት ቀናት ሲሰጥ የነበረዉ ስልጠና በግዢ ሙያ ስነ-ምግባር፣ ሙያዊ መርሆዎች፣ ድንጋጌዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተነግሯል፡፡
በዩኒቨርሲቲዉ የሰዉ ሀብት አስተዳደር ዳይርክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሸዋዬ ጫካ በበኩላቸዉ በተለያዩ የስራ ዘርፎች የሚገኙ ሰራተኞችን ያማከሉ የስልጠና ፕሮግራሞች በየግዜዉ በማዘጋጀት ሰራተኞችን ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ከሳምንት በፊትም ተመሳሳይ ስልጠና ለ35 የፋይናንስ እና ለ20 የግዢና ንብረት አስተዳደር ባለሙያዎች ተሰጥቶ ነበር፡፡