Discussions held on national higher education policy and strategies

ጅማ ዩኒቨርሲቲ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም
*****************************************
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ሀገር በቀል እዉቀትን በማጎልበት ሀገሪቱን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችሉ ተገለፀ፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና መሪ ዕቅዶች ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በትላንትናዉ እለት ዉይይት አካሂዷል፡፡
ዉይይቱን አቅጣጫ በማስያዝ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ እንደተናገሩት የዉይይቱ አላማ ከከፍተኛ እስከ ታችኛዉ ስራ መዋቅር ባሉ ሰራተኞች መካከል የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ፣ በተቋማት መካከል ወጥነት ያለዉ አሰራርን ማስፈን እና የማሻሻያ ሃሳቦችን በግብዓትነት መሰብሰብ ነዉ፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ጠንካራና ዘርፉን በብቃት ለመምራት የሚያስችሉ እንዲሆኑ የሁሉም አስተዋፅዖ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ አክለዉ ገልፀዋል፡፡
የትምህርት ዘርፉ ለቀጣይ አስር ዓመታት የሚመራበት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ፤ በዘርፉ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም የትምህርት ጥራትና አግባብነት እንዲሁም ዜጎችን ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ የሚታዩ ዉስንነቶችን መፍትሄ ይሰጣል ተብሏል፡፡
ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹ በተለይም ሀገር በቀል እዉቀትን በማጎልበት ሀገሪቱን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲያስችሉ ታስበዉ የተዘጋጁ ስለመሆናቸዉ ተነግሯል፡፡
በይይት መድረኩ ላይ የከፍተኛ ትምህርት እና የሳይንስ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንዲሁም የአስር ዓመታት እቅዶችና ቁልፍ የአፈፃፀም መለኪያዎች በዩኒቨርሲቲዉ አመራሮች ቀርበዋል፡፡
የዉይይት መድረኩ ዛሬም ቀጥሎ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች፣ ኢንስቲትዩቶች እና የስራ ክፍሎች በመምህራንና የሰራተኞች ለፖሊሲና ስትራቴጂዉ ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶች እየተሰጡበት ነዉ፡፡