Educational materials supports

ጅማ ዩኒቨርሲቲ መጋቢት 8, 2013ዓ.ም
*****************************************
“ማ/ሰቡ በራሱ ተነሳሽነት የገነባዉ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት አርአያነት ያለውና ሊደገፍ የሚገባ ነዉ” ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፡፡
በመጋቢት 7፣2013 በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመራ ልዑክ በጢሮ አፈታ ወረዳ ዲምቱ ከተማ የሚገኘዉን ነዲ ጊቤ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅትም የተለያዩ የትምህርት መርጃ እና አጋዥ ቁሳቁሶች ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአዳሪ ትምህርት ቤቱ በስጦታ አበርክቷል፡፡
ከስጦታዎቹ መካከል ለተማሪዎች መኝታ አገልግሎት የሚዉሉ አልጋዎች እና ፍራሾች እንዲሁም ኮምፒዉተሮች እና የተለያዩ አጋዥ የትምህርት መርጃ መፅሐፍት ይገኙበታል፡፡
ልዑኩ ከጉብኝቱ ጎን ለጎን ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ ሃላፊዎች፣ ከተማሪ ወላጆች እና ተማሪዎች ጋር በትምህርት ቤቱ ቀጣይ ጉዞ ላይ የፓናል ዉይይት አካሂዷል፡፡
በዚሁ ዉይይት ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ “የተበረከቱት ቁሳቁሶች ባዶ እጃችንን እንዳንመጣ በማለት እንጂ በቂ ሆነዉ አይደለም፤ በቀጣይነት ህብረተሰቡ ትምህርት ቤቱን ለማሳደግ በሚያደርገዉ እንቅስቃሴ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል” ብለዋል፡፡
ተማሪዎችን ለላቀ ስኬት የሚያነሳሱ አነቃቂ ንግግሮችና ዉይይቶች የሚካሄዱበትን መድረክ በማዘጋጀት በዩኒቨርሲቲያችን ባሉ ምሁራን የክህሎትና እዉቀት ሽግግር ለማድረግ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ዝግጁ እንደሆነ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ አክለዉ ገልፀዋል፡፡
በነዲ ጊቤ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ለሚገኝ ልዩ ድጋፍ የሚሻ አንድ ተማሪ የዊልቼር ድጋፍ ይደረግለታል ተብሏል፡፡
ከታች የሚመጡ ተማሪዎችን ለማበረታታት በትምህርታቸዉ የላቀ ዉጤት ለሚያመጡ ተማሪዎች በጅማ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ስኮላር ሺፕ እድል ለመስጠት እንደሚሰራ ታዉቋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በምርምር፣ በፈጠራ፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና በመማር ማስተማር ተግባሮቹ የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ እድገት ለማገዝ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡