ሙስናን ለመከላከል በምርምርና ሳይንሳዊ ትንተና መታገዝ ተገቢ መሆኑ ተገለፀ፡፡
17ኛዉ አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በጅማ ዩኒቨርሲቲ የትውልድ የስነምግባር ግንባታን በጠንካራ ዲሲፒሊን በመምራት ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን በመታገል የብልጽግና ጉዞአችንን እናፋጥናለን በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል፡፡
የአለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በተለያዩ ተቋማት እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሴኔት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ሙሰኝነት ወንጀል፣ ኢ-ምግባራዊ እና የህዝብ አመኔታ ክህደት መሆኑን ተናግረዉ በተለይም እንደ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ አይነት ቀዉሶች ሙስና እንዲስፋፋ አስተዋፅዖ ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል፡፡
ሙስናን በማዉገዝ ብቻ መከላከል ስለማይቻል በምርምርና ሳይንሳዊ ትንተና የታገዘ የፀረ-ሙስና መከላከል ስራ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ጀማል አባፊጣ አክለዉ ተናግረዋል፡፡
በዝግጅቱ የዉይይት መነሻ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ዉስጥ በዓመት ከ75 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች ከህዝባዊ ተቋማት መሰረታዊ አገለግሎቶችን ለማግኘት፣ የፈጸሙትን ወንጀል ለመሰወር፣ የፍትህ አካላትን ትብብር ለማግኘት ጉቦ ይከፍላሉ፡፡
በኢትዮጵያም ሙስና ሰፊ የካፒታል ሽሽት ምንጭ በመሆን የዉጭ ምንዛሪ እጦት በማስከተል ለጥገኝነት እያጋለጠ እንደሚገኝ ተነስቷል፡፡
የስነ-ምግባር መከታተያና ቅሬታ ማስተናገጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ እናኑ ጥላሁን እንደተናገሩት ሃገሪቱ ሙስናን ለመታገል የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች፣ ተቋማት እና እቅዶች ተግባራዊ ብታደርግም ችግሩ ግን የሀገሪቱን የልማት፣ የዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ቁልፍ ችግሮች መንስዔ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎቶቻቸዉ ሙስናን የሚጠየፉ የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎችን ለማነፅ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
ሙስና፣ ግጭቶችና መፈናቀሎች ተመጋጋቢ ችግሮች መሆናቸዉን የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
እንደ ዓለም ባንክ (2018) ጥናት በዓለማችን ላይ በአንድ ዓመት ጊዜ ዉስጥ አንድ ትሪሊዮን የአሜርካን ዶላር በጉቦ መልክ የሚባክን ሲሆን፣2.6 ትሪሊዮን ዶላር በተለያዩ የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ይሰረቃል፡፡
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ደግሞ በየዓመቱ ከ90 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት በሙስና ተሰርቆ ከአህጉሪቱ በህገ ወጥ መንገድ እንደሚወጣ አስታዉቋል፡፡