11ኛው የምርምር ጉባዔ

11ኛው የምርምር ጉባዔ
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሚያዝያ 14/2013ዓ.ም
*********************************
ጅማ ዩኒቨርሲቲ 11ኛውን ዓመታዊ የምርምር ጉባዔ በማካሄድ ላይ ነው።
ጉባዔው “ሀገር በቀል እውቀቶች ለብዝሃነት፣ ለእኩልነት እና ቀጣይነት ላለው እድገት በሚል ሃሳብ ለሁለት ቀናት ይከናወናል።
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ “ጉባዔው ምሁራንን፣ ተመራማሪዎችን እና ባለድርሻ አካላትን በአንድ በማምጣት አሳቦችን በማንሸራሸርና ለሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ከፍ ያለ ሚና አለው”ብለዋል።
ዶ/ር ጀማል አባፊጣ አክለው ለሀገር በቀል እውቀቶች ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በምርምር ታገዞ ጥቅም ላይ በማዋል ብዝሃነትን ማስተናገድ፣ ልማትን ማረጋገጥ እና የሀገር ግንባታ ሂደትን ማሳለጥ እንደሚያስችሉ ገልፀዋል።
ለሁለት ቀናት በመካሄድ ላይ በሚገኘው ዓመታዊ የምርምር ጉባዔ በጅማ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን የተዘጋጁ 80 የምርምር ስራዎች በመቅረብ ላይ ናቸው።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ተስፋዬ ገበየሁ በበኩላቸው ሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀም እና ሳይንሳዊ የምርምር ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ልማት ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል።
እንደ ም/ፕሬዚደንቱ ገለፃ ሀገር በቀል እውቀቶች በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔን ለማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና አላቸው።
ጉባዔው ምሁራኑ ሀሳቦችን እንዲያንሸራሽሩና በብዝሃነት፣ እኩልነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አተያይ የሚለዋወጡበት እንዲሁም ተሞክሮች የሚቀመሩበት እንደሆነ ይጠበቃል።
የጅማ ዩኒቨርሲቱ ሴኔት አባላት፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ፅሁፍ አቅራቢዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በዓመታዊ የምርምር ጉባዔው ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።