በሰራተኞች ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ያለመ የመግባቢያ ሰነድ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፣ በጅማ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ በኩል አቶ ፀጋዬ አብዲሳ እና በጅማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኩል ደግሞ አቶ መሀመድኑር አባዱራ ተፈርሟል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ትስስር በቴክኖሎጂ፣ በምርምር፣ በመማር ማስተማር፣ በፈጠራ እና በማህበረሰብ አገልግሎት ሊጠናከር ይገባል ተብሏል፡፡
በመግባቢያ ሰነዱ መሰረት የ (SWAP) ወይም የክፍያ ልዉዉጥ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆቹ ሰራተኞች በጅማ ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርት እድል የሚያገኙ ሲሆን በጅማ ዩኒቨርሲቲ በዝቅተኛዉ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ የአስተዳደር ሰራተኞች ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆቹ ወደ ዲፕሎማ እንዲያድጉ ጥሩ የስራ አፈፃፀም ያላቸዉ የአስተዳደር ሰራተኞች የትምህርት እድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕረዝደንት ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ገልፀዋል፡፡
በልዉዉጥ የማስተማሩ ተግባር የገንዘብ ክፍያን የሚጠይቅ ባለመሆኑ አሰራሩን ቀላል እና ዉጤታማ እንደሚያደርገዉ ታምኖበታል፡፡ በልውውጥ የማስተማሩ ሂደት በያዝነው አመት የሚጀመር ነው።
በዚህም መሠረት 8 የጅማ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ሠራተኞች በ መጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም በአካውንቲንግ፣ ማኔጅመንት እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማስተርስ ፕሮግራም ደግሞ 3 ሠራተኞች አካውንቲንግ እና በማኔጅመንት እድሉን እንደሚያገኙ ተገልፅዋል። ከጅማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሎጅ ደግሞ፣ በማስተርስ እና በዲግሪ ፕሮግራሞች በማኔጅመንት እና በሲቪል ኢንጂነሪንግ 2 ሠራተኞች በዩኒቨርሲቲው የትምህርት እድል ያገኛሉ ተብሏል።
በምላሹም 30 የጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሠራተኞች 25 በሆቴልና ቱሪዝም፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በአካውንቲንግ በጅማ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ትምህርት የሚሰጣቸው ሲሆን በጅማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ደግሞ 5 ሠራተኞች በአውቶሞቲቭ ኢንጂን ሠርቪስ፣ በሳኒተሪ ኢንስታሌሽን፣ በቢውልዲንግ ኤሌክትሪካል ኢንስታሌሽን እና በኤሌክትሮኒክስ ሙያ ስልጠና ይሰጣቸዋል። ይህም የሠራተኞችን ጥቅምና ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያግዝ ብሎም በተቋማት ደረጃ ትስስርን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ተብሏል።
የተቋማትን ራዕይ እና ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ የሰዉ ሃይል ልማት ቁልፍ በመሆኑ የመግባቢያ ሰነዱ ያለዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተጠቅሶ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ለዚሁ ስኬት ይሰራል ተብሏል፡፡
ወደፊት ጅማ ዩኒቨርሲቲ መሰል ትስስሮችን በማጠናከር እስከታችኛዉ የትምህርት መዋቅር ድረስ ካሉ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑ ታዉቋል፡፡