ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለወገን የሚያደርገዉን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ዛሬም በጅማ ከተማ የተባበሩት አካባቢ በቀድሞ አጠራሩ ኢዲዲሲ ዉስጥ ለሚኖሩ ከ 450 በላይ አባወራዎች ፍራሾች፣ ምግብና ምግብ ነክ እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዉ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሁኔታ እና አጋጣሚዎች ለህብረተሰቡ የተለያዩ ድጋፎችን ያደረገ ሲሆን በዛሬዉ እለትም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክስ እና አስተዳደር ሰራተኞች ድጋፍ ግምታቸዉ ከ 500 ሺህ ብር በላይ የሆኑ ፍራሽ፣ የምግብ እህልና ግብዓቶች፣ የንፅህና መጠበቂያን ለተጠቀሱት ተረጂዎች አስረክቧል፡፡

በድጋፍ አሰጣጡ ፕሮግራም ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፣ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ፣ የጅማ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ካሳሁን ጆብር እና የከተማዉ ብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ አቶ ለታ አሸብር ተገኝተዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ይህ ድጋፍ ግዜያዊ ችግርን ለመቅረፍ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን ተናግረዉ፤ መንግስት እነዚህን ወገኖች በዘላቂነት ማቋቋም እንዳለበት በመጠቆም ለዚህም ተግባራዊነት ዩኒቨርሲቲዉ የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ ወደፊትም በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎቶቹ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግና በተመሳሳይ ችግር ዉስጥ ያሉ ወገኖችን ለመርዳት ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ጀማል አባፊጣ አክለዉ ገልፀዋል፡፡
የምግብና ምግብ ነክ እንዲሁም ፍራሾችና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ተረጂዎቹ በተወካዮቻቸዉ አማካኝነት ተረክበዋል፡፡