ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለፕሬዝዳንትነት ቦታ ብቃቱና ፍላጎት ያላቸዉ አመልካቾች እንዲወዳደሩ ጥር 24/2011 ዓ.ም በተለያዩ ሚዲያዎች ባወጣዉ ግልጽ ማስታወቅያ መሰረት አመልካቾች መረጃቸዉን በማስገባት በተለያዩ ደረጃዎች ዉድድር ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል::
በምርጫ ሂደቱም ከ250 በላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የዩቨርሲቲዉ ሴኔት እና የስራ አመራር ቦርድ በቀን 01/07/2011 ዓ.ም. የቃለ-መጠይቅ ፓናል በማካሄድ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩና ማጣሪያዎችን አልፈው የደረሱ 9 እጩዎችን በመገምገም 5 እጩዎችን ለዩኒቨሲቲዉ የስራ አመራር ቦርድ አስተላልፏል፡፡ የዉድድሩ ሂደት የተመራዉ የሳይንስና ከፍተኛ ት/ት ሚኒስቴር ባወጣዉ መስፈርት ሲሆን ሂደቱን ለመምራት አምስት ሰዎችን የያዘ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየደረጃዉ ግምገማ ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡ ኮሚቴዉ ከቦርድ አባላት፣ ከሴኔት አባላት፣ ከተማሪ፣ ከመምህራን እና ከአስተዳደር ሰራተኞች ተወካይ የተዉጣጣ ሲሆን የዉድድር ማስታወቂያ ከማዉጣት ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲዉ የስራ አመራር ቦርድ ጉባኤ የሂደቱን ዉጤት እስከ ማሳወቅ ድረስ በትጋት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በዚሁ መሰረት የዩኒቨርሲቲዉ የስራ አመራር ቦርድ ሚያዚያ 02/2011 ዓ.ም ባካሔደው ልዩ ጉባኤ 3 እጩዎችን (ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፣ ፕሮፌሰር አርጋዉ አምበሉ እና ዶ/ር ናቃቸዉ ባሹን) በእጩነት ለሳይንስና ክፍተኛ ት/ት ሚኒስቴር ኣቅርቧል:: የሳይንስና ክፍተኛ ት/ት ሚኒስቴርም ዶ/ር ጀማል አባፊጣን ከሚያዚያ 11/2011 ዓ ም ጀምሮ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል፡፡
ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የዩኒቨርሲቲዉ ነባር መምህር እና ተመራማሪ ሲሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች በዩኒቨርሲቲውና ከዩኒቨርሲቲው ውጭ በሃላፊነት ያገለገሉና በአሁኑም ወቅት የማህበረሰብ አገልግሎት ቢሮ ዳይሬክተር ሆነዉ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
የዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰብ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ለዚህ ሃላፊነት በመመረጥዎ የተሰማዉን ልባዊ ደስታ እየገለጸ መልካም የስራና የስኬት ዘመን እንዲሆንልዎ ይመኛል፡፡
ስለ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ይህን አገናኝ በመጫን ሙሉ መረጃ ማግኘት ይችላሉ፡፡
ሚያዚያ 11/2011 ዓ.ም
ጅማ ዩኒቨርሲቲ