ዲጂታል ጅማ

ዲጂታል ጅማ
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነሐሴ 18/2013ዓ.ም
*************************************
የቡና ምርት እና ስርዓተ ግብይት፣ የፈጠራ ዉጤቶችን ወደ ገበያ ማስገባት እና ለተመራቂ ተማሪዎች የስራ እድል ማመቻቸት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዲጂታል ጅማ የተሰኘ የልህቀት ማዕከል በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተቋቋመ፡፡
የተመሰረተው የልህቀት ማዕከል በሀገሪቱ የመጀመሪያው ሲሆን ጅማ ዩኒቨርሲቲን በቀዳሚነት በማስቀመጥ በሀገሪቱ የሚገኙ መሰል ተቋማት የአተገባበር ክህሎትና ልምድ እንዲያገኙ በማድረጉ በኩል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የልህቀት ማዕከሉን ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ወርክሾፕ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ተካሂዷል፡፡
ወርክሾፑ በኦንላይን ገንዘብ ልውውጥ (ክሪፕቶ ከረንሲ) ግንዛቤ መፍጠር፣ ባለድርሻ አካላትን መለየት፣ የፓይለት ፕሮጀክት ትግበራ ቦታ ልየታ እና የፕሮጀክት ትግበራ ዘዴዎችን መለየትን ዓላማ ያደረገ ሲሆን በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ በአፍሮ ቫሊ እና በጅማ ዞን አስተዳደር በትብብር የተዘጋጀ ነው፡፡
ግብርናን በቴክኖሎጂ ማዘመን እና የተመራቂዎችን የመቀጠር እድል ማጎልበትን አላማ ያደረገ የመግባቢያ ሰነድ በጅማ ዩኒቨርሲቲ አፍሮ ቫሊ እና ጅማ ዞን ተፈራርመው ሲሰሩ መቆየታቸዉ ተገልፅዋል፡፡
ወርክሾፑ በነበረው የሁለት ቀናት ቆይታ የፈጠራ ባለሙያዎችን በኦንላይን የገንዘብ ልውውጥ ዘዴ ገበያ እንዲፈጠርላቸዉ ማድረግ እና የተማሪዎችን የመቀጠር አቅም ለማሳደግ የስራ ፈጠራን ማበረታታት ላይ ያተኩረ ነው፡፡
በተጨማሪም በግብርናዉ ዘርፍ በተለይም በቡና ምርት እና ሽያጭ ሂደት ላይ ያለውን ክፍተት በማጤን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ቀላል እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሰራርን መፍጠር ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
ዲጂታል ጅማ የልህቀት ማዕከል መመስረት በቡና ምርትና የገበያ ትስስር ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ዉስብስብ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ አማካኝነት ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ያደርጋል ተብሏል፡፡
የፈጠራ ባለቤቶችን ስራዎች ወደ ገበያ በማስገባት የአገልግሎት ሰጪ እና ተጠቃሚ ግንኙነትን ለማጎልበት እና የተመራቂ ተማሪዎችን የመቀጠር እድሎችን ለማስፋፋት ቀጣሪ ተቋማትን እና ተማሪዎችን የሚያስተሳስር ስርዓት በመፍጠሩ ረገድም የልህቀት ማዕከሉ መመስረት እጅጉን እንደሚጠቅም ተወስቷል፡፡
በወርክሾፑ ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከጅማ ዞንና ከተማ ቢሮዎች የተውጣጡ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ነበሩ፡፡