የጅማ ዩኒቨርሲተ ከፍተኛ አመራሮች የቴክኖሎጂ መንደር ጉብኝት

በሀገራችን ኢትዮጵያ የስንዴ ፍጆታን በሀገር ዉስጥ ምርት ለመሸፈንና ከዉጭ የሚገባዉን ለማስቀረት ከቅርብ ግዜ ወዲህ በስፋት እየተሰራ ይገኛል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲተ ከፍተኛ አመራሮች በዴዶ ወረዳ ኢላላ ቀበሌ በሚገኙ አርሶ አደሮች በክላስተር የለማ የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል፡፡ዩኒቨርሲቲው በጅማ ዞን አምስት ወረዳዎችን በመምረጥ የቴክኖሎጂ መንደር በማቋቋም ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የዩኒቨርሲቲዉ ግብርናና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ሳነቴ የተባለ የዋግ በሽታን ተቋቁሞ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ የስንዴ ዘር ለአርሶ አደሮቹ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በምርት ሂደቱ ላይ በሽታ እና ነብሳት ቢከሰቱ ምላሽ የሚሰጥ የባለሙያዎች ቡድን በኮሌጁ ተቋቁሞ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ሲወጣ እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡
የምርቱን ዉጤት የተመለከቱ በአካባቢዉ የሚኖሩ ሌሎች አርሶ አደሮች ዘሩን በመግዛት በስፋት እያመረቱ መሆኑን በመስክ ምልከታዉ ተረጋግጧል፡፡
አርሶ አደሮቹም በዉጤቱ ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀዉ በአካባቢዉ የአፈር አሲዳማነት በመኖሩ ችግሩን ተቋቁመዉ ምርታማ እንዲሆኑ የሚመለከታቸዉ አካት ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቀበሌዋ እየተከናወነ የሚገኘዉ የከብቶች ማዳቀል ስራም የተጎበኘ ሲሆን የዴዶ ወረዳ ከጥቂት አመታት በኋላ የሀገሪቱ የወተት ምርት ኮሪዶር ሊያደርጋት የሚያስችል ዉጤት እየተመዘገበ ነዉ ተብሏል፡፡
የከተማ ግብርና እንቅስቃሴም በጉብኙቱ የተካተተ ሲሆን የጅማ ከተማ ነዋሪዎች በግቢያቸዉ በሚገኝ አነስተኛ ስፍራ ላይ የጓሮ አትክልቶችን እያመረቱ ወዲህ ለራስ ፍጆታ ወዲያ ደግሞ ለገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ በከተማዋ ለሚኖሩ 30 አባወራዎች ለእያንዳንዳቸው የጓሮ አትክልቶች ዘር እና አስር አስር ዶሮዎችን ድጋፍ አድርጓል፡፡
የምርቱን ዉጤት ያዩ ሌሎች ነዋሪዎችም የከተማ ግብርናን በማስፋፋት ላይ ናቸዉ፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲም የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻልና ምርታማ እንዲሆን ብሎም የከተማ ግብርና እንዲስፋፋ የሚደረገዉን ጥረት ለማሳካት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡