በኦሮሞ ፍክሎርና ስነ-ፅሁፍ እና ታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍሎች ለጅማ ዞን ባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች በባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ማሰባሰብና ማስተዳደር ዘዴ ላይ ስልጠና እየተሰጠ ነዉ፡፡
በስልጠናዉ መጀመሪያ ላይ የጅማ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ጫልቱ አወል እንዳሉት ጅማ ዩኒቨርሲቲ የቢሯችንን እንቅስቃሴ መደገፍ በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነዉ ብለዋል፡፡
በባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ምንነት፣ አሰባሰብ እና አያያዝ ላይ ክፍተቶች አሉ ያሉት ወ/ሮ ጫልቱ ይህ ስልጠና ክፍተቶችን ለመድፈንና አካባቢያችን ብሎም ሀገራችን ከዘርፉ ልታገኝ የምትችለዉን ጥቅም እንደሚያሳድግ ገልፀዋል፡፡ ሰልጣኞችም ከዚህ ስልጠና የሚያገኙትን እዉቀት በተግባር ለማዋል እንዲተጉም መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
የሶሻል ሳይንስና ሂዉማኒቲስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቀናቴ ወርቁ በስልጠናዉ መክፈቻ ላይ እንዳሉት በጅማ ዞን በሚገኙ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ላይ በርካታ ጥናቶች የተሰሩ ሲሆን ጥናቶቹም በቅርስ አሰባሰብ፣ አያያዝና አስተዳደር ዙሪያ ክፍተኛ ክፍተት እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡
ለነዚህ ክፍተቶች መፍትሄ በመሻትም ኮሌጁ ካለፈዉ አመት ጀምሮ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ ጠቅሰዉ በ2008 ዓ.ም በ (DDTP) ፕሮግራም ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የት የት አካባቢ እንዳሉ ተለይተዉ መታወቃቸዉን ዶ/ር ቀናቴ ተናግረዋል፡፡
በኮሌጁ ያለዉን ሳይንሳዊ እዉቀት ተጠቅሞ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚታየዉን የቅርሶች አሰባሰብ፣ አያያዝ እና አጠቃቀም ክፍተት ለመድፈንና ቅርሶቹን ለማስተዋወቅ፣ ለማልማት ብሎም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች እንዲኖሩት ለማድረግ ስልጠናዉ ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚኖረዉ ታዉቋል፡፡
ዶ/ር ቀናቴ እንዳሉት ሰዎች እንደ ጅማ አባጅፋር ቤተ-መንግስት፣ ሙዚየም፣ ሰቃ ፏፏቴ እና ሌሎች ቅርስችን ያዉቋቸዋል እንጂ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ብዙም ግንዛቤዉ ስለሌላቸዉ የሀገር ዉስጥ ጎብኚዎችንም ቁጥር ለማሳደግ መሰራት አለበት፡፡ ወደፊትም በኮሌጁ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ዘርፉን ለማሳደግ ቀጣይነት ያለዉ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናዉ በኦሮሞ ፎክሎርና ስነ-ፅሁፍ እና ታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍሎች እየተሰጠ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በርካታ የጅማዞን ባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡