የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር ለዓባይ
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ግንቦት 9/2013ዓ.ም
*************************************
ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀት ክፍተቶችን በመሙላት እና የሳይንሳዊ መረጃ ጉድለቶችን በማስተካከል ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ፤ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የዩኒቨርሲቲዎች ሚና ላይ ያተኮረ የዉይይት መድረክ የዩኒቨርሲቲዎች ትብብርና የሳይንስ ዲፕሎማሲ ለዓባይ ዘላቄታዊ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት በሚል መሪ ሀሳብ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ለዉይይት መነሻ የሆኑ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች እና የጥበብ ስራዎች ቀርበዋል፡፡
ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ፣ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ፣ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፣ ኢንጂነር ማሙዬ ቡሴር፣ አቶ ኤፍሬም ዋቅጅራ እና አቶ አብዮት ደስታ በህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ቴክኒካል ጉዳዮች፣ በግድቡ ዙሪያ ስለሚቀርቡ ሀሰተኛ ወቀሳዎች፣ ፖለቲካዊና ህጋዊ ጉዳዮች፣ ስለ ግድቡ የዉሃ አሞላል እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን የተመለከቱ ፅሁፎችን አቅርበዋል፡፡
የዉይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ “እንደ ድንበር ተሻጋር ወንዞቻችን ሁሉ ሳይንስም ድንበር የለዉም በማለት፣ በዩኒቨርሲቲዎች እና በምርምር ተቋማት ያሉ የአካዳሚያ አባላት፣ ሳይንቲስቶች እና ተመራማሪዎች በአባይ ወንዝ ዙሪያ የነበሩና አሁንም ያሉ የዘመናት ኢ-ፍትሃዊነት እና የተፋሰሱ አገሮችን የአንድ ወገን ፖሊሲ በማጤን ሳይንሳዊ መፍትሔ መተለም አለባቸው’’ ብለዋል፡፡
የፐብሊክ ዲፕሎማሲን ለማጎልበት መሰል የዉይይት መድረኮችን ማጠናከር እንደሚገባ የተናገሩት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፤እንደ አባይ ወንዝ ያሉ የጋራ ሀብቶች ሰላማዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ መዋላቸው የሚረጋገጠዉ በእውቀትና ሳይንስ ሲደገፍ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረጉ ስምምነቶች ላይ ይደርሱ ዘንድ ዩኒቨርስቲዎች እውቀትንና ሳይንስን መሰረት ያደረጉ የህዝብ-ለህዝብና የምሁራን መስተጋብርን የሚፈጥሩና የሚያጠናክሩ መድረኮችን መፍጠር እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የዓባይ ወንዝ ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የትዉልዶች የዘመናት ጥያቄ እንደሆነ ገልፀዉ በታችኛዉ የተፋሰስ ሀገራት ሳይንሳዊ ያልሆኑ ጥናቶችን በማዘጋጀት ሰላማዊና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸዉ ዩኒቨርሲቲዎች ተባብረዉ በሳይንስ ዲፕሎማሲ የተደገፉ ሀቆችን ለዓለም የማሳየት ስራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በቀረቡት የዉይይት መነሻ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ የመድረኩ ታዳሚዎች ሰፊ ዉይይት አድርገዋል፡፡ መድረኩ የተለያዩ በሳይንስ የተደገፉ ሀቆች የቀረቡበት እንደሆነና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና በዩኒቨርሲቲዎች ሚና ላይ ያተኮረዉ መድረክ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ቀደም ሲል ሲዘጋጁ የነበሩት መድረኮች አካል ሲሆን የሀገር ዉስጥና ዓለም አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎችን ትብብር ለማጠናከር አልሞ የተዘጋጀ ነዉ፡፡
በመድረኩ ላይ ስለ ዓባይ ፍትሃዊ፣ ዘላቂና ሰላማዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ያጎሉ የጥበብ ስራዎች የጅማ ዩኒቨርሲቲ አምባሰደር በሆነችው ተማሪ ስምረት ዓቢዩ እና ተማሪ በዛብህ ቀርበዋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደ ከፍተኛ ት/ት ተቋም ከሚጠበቅበት የመማር ማስተማር የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮዎቹ በተጨማሪ መሰል ሀገራዊ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ የበኩሉን ይወጣል ተብሏል፡፡
ከፌደራል እና ከኦሮሚያ ክልል መንግስት፣ ከጅማ ዞን እና ጅማ ከተማ፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚደንቶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ካዉንስል አባላት፣ ፕሮፌሰሮች፣ ከተማሪዎች ህብረት እና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች የዉይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡