(ጅማ ዩኒቨርሲቲ መስከረም 13፣ 2013ዓ.ም) የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ምስጋና አቀረቡ።
ፕሬዝደንቱ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ለሶስት ቀናት በዩኒቨርሲቲው ሲካሄድ በቆየው የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ማስቀጠልና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ የተሠሩ የፈጠራ ስራዎች ዓውደ ርዕይ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው።
ለዚህ ፕሮግራም ስኬታማነት የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሃላፊነቶችን በመውሰድ ሲሰሩ ቆይተዋል።
ዶ/ር ጀማል ስኬቱን ከአድካሚውና አስቸጋሪው የማራቶን ውድድር ጣፋጭ ስኬት ጋር ባገናኙበት ንግግራቸው እንዳሉት ረዘም ያለ ግዜ ሊወስድ የሚችለውን ስራ በአንድ ሳምንት ውስጥ አጠናቀን ዩኒቨርሲቲያችንን ከፍታ ላይ ማድረሳችን አስደስቶኛል፤ ሁሉም ሰው በስኬቱ ሊኮራ ይገባዋል ብለዋል።
ይህንን ስኬት ልናከብር ይገባል፣ በዝግጅቱ የታየውን የአንድነት፣ የመተሳስብ እና ለአንድ አላማ በጋራ የመቆምን የትብብር መንፈስ ማስቀጠል ተገቢ እንደሆነ ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን፤ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምላሽ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለዓውደ ርዕይ ያቀረባቸው የፈጠራ ስራዎች የብዙሃኑን ትኩረት የሳቡ በመሆናቸው ለቀጣይ ስኬት እራሳችንን ማዘጋጀት አለብን ሲሉም ዶ/ር ጀማል አክለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ኮንፍራንሶችን በብቃት እንደሚወጣ ያሳየበት ትልቅ ዝግጅት በመሆኑ ሰንዶ በማስቀመጥ በቀጣይነት እንደ ማጣቀሻ እንዲያገለግል ማድረግ እንደሚገባ በተሳታፊዎች ተነስቷል።
ዩኒቨርሲቲውን በአለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ተቋማት እንደ አንዱ ማየት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ማሳያዎቹ የምሁራኖች የጥናትና ምርምር ውጤቶች በአለም አቀፍ ጆርናሎች መታተማቸውና ለአለም አቀፉ ማህበረሠብ ጥቅም መስጠት መቻላቸው እንደሆነ ተጠቅሷል።
ባስመዘገብነው ስኬት ሳንዘናጋ ዩኒቨርሲቲውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ይበልጥ መትጋት እንደሚያስፈልግ የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንቶች የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችንና የመንግስት ተቋማትን ምላሽ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ሁሉም እንግዶች በሚባል ደረጃ በቆይታቸው ባዩት ነገርና በዝግጅቱ እንዲሁም በጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ቅንጅት መገረማቸውንና ምስጋና ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሰራተኞች መካከል የታየው የመደማመጥና የመደጋገፍ ባህል ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከታች እስከ ላይ ባለው መዋቅር ሀገር አቀፍ ዝግጅቱን በተሳካ ሁኔታ ያዘጋጁ አባላት የሚሳተፉበት ልዩ ፕሮግራም በቅርቡ እንደሚካሄድ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል ተናግረዋል።
በድህረ-ፕሮግራም ውይይቱ ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንቶች፣ የሴኔት አባላት እና የፕሮግራሙ ዝግጅት ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።