የኮቪድ-19 ክትባት
ጅማ ዩኒቨርሲቲ መጋቢት 29/2013 ዓ.ም
****************************************
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ-19 ክትባት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሄደ፡፡
መርሀ ግብሩን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ክትባቱን በመዉሰድ አስጀምረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲዉ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ተስፋዬ ገበየሁ የዩኒቨርሲቲዉን ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣን በመወከል በመርሀ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “ኮቪድ-19 ወደ ሀገራችን ከገባ ግዜ ጀምሮ በርካታ ችግሮችን አስተናግደናል ከነዚህም ዉስጥ የትምህርት መቋረጥ እና በቂ ምርመራ አለማድረግ ዋነኞቹ ነበሩ” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ አክለዉም መልካም አጋጣሚዎችን ያነሱ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አባላት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ በሺዎች ለሚቀጠሩ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እንዲሁም ለተማሪዎች የሳይኮ ሶሻል ስልጠና እና ሌሎች ተግባራት ስኬቶች መሆናቸዉን ገልፀዋል፡፡
በጅማ ህክምና ማዕከል በሽታዉን ለመከላከል ቅድሚያዉን በመዉሰድ ለኮቪድ-19 ተጠቂዎች የህክምና እርዳታ በመስጠት ላይ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በመሰጠት ላይ ነዉ፡፡
የኮቪድ-19 በሽታ ወደ ሀገራችን ከገባበት ግዜ አንስቶ እስካሁን ባሉት ጊዜያት የጅማ ድንገተኛ አደጋ ክወና ማዕከል ከ30 ሺህ በላይ ምርመራዎችን ያደረገ ሲሆን አንድ ሺህ አንድ መቶ የኮሮና ተጠቂዎች ተገኝተዋል፡፡
ከነዚህ ዉስጥ ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንቱ (288) ወደ ህክምና ገብተዉ ሁለት መቶ አስራ ስድስቱ (216) አገግመዋል፤ 40 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸዉ አልፏል፡፡
የኮቪድ-19 በሽታ አሁንም ስጋት በመሆኑ ማህበረሰቡ የመከላከል ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡