የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርካቶ፣ ሚኒስትር ዲኤታዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ እና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንቶች አረንጉዋዴ አሻራቸውን በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ችግኝ በመትከል አሳርፈዋል።
የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙን በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ እምዬ ቢተው እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኡባ አደም ለምክር ቤቱ በተዘጋጀው ስፍራ ላይ ችግኝ በመትከል አስጀምረውታል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ በችግኝ ተከላው ወቅት እንደተናገሩት ለሁለም ተቋማት አራት አራት ችግኞች የሚተክሉበት ቦታ መዘጋጀቱን ገልፀው ይህ ቦታ የወንድማማችነት፣ የፍቅር እና የሠላም አደባባይ ይሆናል ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ አክለውም ቦታው ወደፊት ተማሪዎች የሚዝናኑበት፣ ልምድ በመውሠድ አካባቢያቸውን የሚያስውቡበትና በወንድማማችነት እንዲሁም በአብሮነት የሚያሳልፉበት እንደሚሆንና የችግኝ ተከላው ተሳታፊዎች ዩኒቨርሲቲው ቤታቸው በመሆኑ ባሻቸው ግዜ መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
ችግኞችን የመንከባከቡን ስራ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሃላፊነት የሚወስድና ስራውን የሚያስቀጥል እንደሆነ ተጠቁሟል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የተፈጥሮ ሚዛን ጥበቃ ጥሪን ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ የችግኝ ተከላ ፕሮግራሞች ሲካሄዱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በነበረው የከፍትኛ ትምህርት ማስቀጠል ጉባዔ እና የኮቪድ-19 ምላሽ የተሠሩ የፈጠራ ስራዎች ዓውደ-ርዕይ ተሳታፊዎች የንጉስ አባጅፋርን ቤተ- መንግስት ጎብኝተዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ኦፊሻላዊ የቴሌግራም ገጻችን አባል ይሁኑ፤