የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በዩኒቨርሲቲው ህክምና ማዕከል ጉብኝት አደረጉ።

የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ከዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት አባላት ጋር በመሆን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የካንሠር ህክምና መስጫ ማዕከል፤ አዮ የተቀናጀ አምቡላንስ አገልግሎት፤ የኦክስጅን ማምረቻ፣ ማጣሪያና ማስተላለፊያ ፕላንት፤ የጅዩ-ሲምቦና ህክምና ቁሳቁስ ዲዛይን ላብራቶሪ እና በባዮሜዲካል ማዕከል የሚገኙ የፈጠራ ስራዎች በጉብኝቱ ምልከታ ከተካሄደባቸው መካከል ናቸው።

ሚኒስትር ድኤታው በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው አዮ የአንድ ማዕከል የአምቡላንስ አገልግሎት መጀመር የሚያበረታታ መሆኑን ገልፀው ወደፊት መሰል አገልግሎቶችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር መሀመድ መጫ የዩኒቨርሲቲው የካንሰር ህክምና ማዕከል ስራ መጀመር የሚያስችል ዝግጅትን እያጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመቀጠል ለሀገራችን ሁለተኛው ተቋም ሆኖ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተናግረዋል።

ማዕከሉ አገልግሎት ሲጀምርም አገልግሎቱን ለሚሹ ዜጎች ጊዜን የሚቆጥብ እንዲሁም ለህክምና የሚደረግ የባህር ማዶ ጉዞንና ገንዘብን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ የሚያስችል እንደሚሆን ተነግሯል።

ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የካንሰር ህክምና ልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያደርገውን ጉዞ ማስቀጠል አለበት ብለዋል።

የኦክስጅን ማምረቻ ፕላንቱን በቀን እስከ 120 ሲሊንደሮችን መሙላት በሚያስችል መልኩ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝም በጉብኝቱ ወቅት ተነስቷል።

ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በጤናው ዘርፍ እያበረከተ ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ስለሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ልምድ የተወሠደበት መሆኑን ተናግረው ሂደቱን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በጉብኝቱ ወቅትም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘደንት ፣ ም/ፕሬዘደንቶችና የሴኔት አባላት የህክምና ማዕከሉ በበቂ ሁኔታ ሃገራዊ አገልግሎቱን በሚያሳድግበት ጉዳይ እና በባዮሜዲካል ማዕከል የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች በሚስፋፉበት አቅጣጫ ላይ ከዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡