የአዮ የተቀናጀ የአምቡላንስ አገልግሎት ለድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ።

(ጅማ ዩኒቨርሲቲ መስከረም 16፣2013 ዓ.ም) የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤን በማሻሻል የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ማዘመን የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ሆነ።

የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም ማስጀመሪያ ዝግጅት በጅማ ዩኒቨርሲቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል።

አዮ አምቡላንስ (እናት አምቡላንስ) አገልግሎትም ስራውን በይፋ ጀምሯል። የአምቡላንስ አገልግሎቱ በጅማ ከተማ እና ዞን የሚገኙ ሁሉም አምቡላንሶች በአንድ ማዕከል ስር ሆነው አገልግሎት የሚሰጡበትን አሰራር የያዘ ነው።

አዮ የአምቡላንስ አገልግሎት በኮምፒወተር የታገዘ በመሆኑ አምቡላንሶችን በጂ.ፒ. ኤስ ትራክ በማድረግ ህብረተሠቡ በ6238 በሚያደርገው ጥሪ መሠረት የትኛው አምቡላንስ በቅርበት እንዳለ ለይቶ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ነው። ይህንንም ለመፈፀም የሚረዳ ዲስፓች (ምላሽ ሰጪ) በጅማ ህክምና ማዕከል እንደሚኖርም በዝግጅቱ ተገልጿል።

የአምቡላንስ አገልግሎቱ የተሟላ የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንደሆና አገልግሎቱንም በ6238 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ይህ የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም ጅማ ከተማ እና ዩኒቨርሲቲውን ከሚያገናኙ በርካታ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው በመሆኑ የጤናው ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች ለማሻሻል ትልቅ እንድምታ ያለው ነው ብለዋል።

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻል ፕሮግራምን እውን በማድረጉ ረገድ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን አድርጉዋል፤ በማድረግላይም ይገኛል ሲሉ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አክለዋል።

ለፕሮግራሙ ተግባራዊነትና ስኬት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ጅማ ከተማ በጋራ እየሰሩበት ይገኛሉ።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር መሀመድ መጫ ፕሮግራሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ በስድስት ከተሞች የሚተገበር መሆኑን ገልፀው በጤና ሚኒስትር የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤን ማሻሻል በሚል ንቅናቄ የተጀመረና እንደ ቀይ መስቀል፣ እሳት አደጋ፣ የግልና የመንግስት ጤና ተቁዋማት፣ መድሃኒት ቤቶች፣ የዞንና ከተማ መስተዳድሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በጋራ የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ ድንገተኛ ህክምናና ሪፈራል ሲስተምን ለማዘመንና የተቀናጀ አገልግሎትን በመስጠት በማህበረሰቡ ውስጥ በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ነው።

የጅማ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ቲጃኒ ናስር፣ የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ክቡር አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ፣ የጅማ ከተማና ዞን ልማት ፎረም አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል።