የህክምና አገልግሎት ጥራትን በማሻሻል የዜጎችን ህይወት መታደግ ይገባል ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለፁ፡፡

የጅማ ህክምና ማዕከል የህክምና ጥራት ማሻሻያ እቅድ የመክፈቻ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡ የመክፈቻ መርሀ-ግብሩን ውይይት የጤና ሚኒስትሯ ዶር ሊያ ታደሰ መርተውታል፡፡
ማዕከሉ የለውጡን ጠንካራ ጎን አጠናክሮ በማስቀጠል እና ደከማ ጎኑን ገምግሞ የማስተካከያ እርምጃ በመውስድ ለዚህ ደረጃ መብቃቱ የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ዶር ሊያ ታደሰ የአልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ለማሳደግና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካለት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝነት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና የተማሪዎች ጉዳይ ም/ ፕሬዝዳንት ዶር ቀነኒሳ ለሚ የህክምና ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሙ በጤና ሚኒስቴር አነሳሽነት በሀገሪቱ ባሉ 22 የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የሚተገበር ሲሆን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል አንዱ ነው፡፡
ም/ፕሬዝዳንቱ በመቀጠልም፣ የህክምና ማሻሻያው እቅድ የህክምና ማዕከላችንን አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ይህንን የጥራት ማሻሻያ መሪ እቅድ ለመተግበር የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል ዝግጅቱን አጠናቅቆ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ፕሬዝደንትና የህክምና ማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር መሀመድ መጫ የህክምና ማሻሻያ ፕሮግራሙ በሀገራችን የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ ዘመናዊ የጤና አገልግሎት ለመተግበር እና የዘርፉን ተዋናዮች ለማሳተፍ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ስለ ህክምና ጥራት ማሻሻያ እቅዱ ማብራሪያ በቺፍ ክሊኒካል ዳይርክተሩ በዶ/ር አህመድ መሀመድ የቀረበ ሲሆን ከተሳታፊዎችም ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ከተነሱት አስቴቶች መካከል፣ የጤና ሚኒስቴር የበጀት አመዳደቡን እንዲከልስ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ያለዉ ትብብር፣ የበጀት ዝቅተኝነት እና ከግዢ ጋር በተያያዘ ያለዉ መዘግየት ዋና ዋና ናቸዉ፡፡
በተለይም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል ለደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ አጎራባች የደቡብ ክልል ወረዳዎች፣ ጋምቤላ እና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ አገልግሎት የሚሰጥ ግዙፍ ተቋም በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ድጋፍ ሊደረግ ይገባልም ተብሏል፡፡
ከተሳታፊዎች ጋር የተደረገዉን ዉይይት የመሩት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የተነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዉ ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን ለተነሱ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት እንደሚሰሩም አሰረድተዋል፡፡
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ም/ሃላፊ ዶ/ር ጉሻ ባላኮም ቢሯቸዉ በትብብር እንደሚሰራ እና ለተነሱ ችግሮች የመፍትሄ አካል ለመሆን ዝግጁ እንደሆነ በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰን ጨምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአጠቃላይ ህክምና አገልግሎት ጀነራል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ያዕቆብ ሰማን፣ የህክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አባስ ሀሰን፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ም/ሀላፊ ዶ/ር ጉሻ ባላኮ እንዲሁም ከጅማ ከተማ እና ዞን በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡