ወደ ዕውቀት-መር ኢኮኖሚ

ወደ ዕውቀት-መር ኢኮኖሚ
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሀምሌ 5/2013 ዓ.ም
*************************
የከፍተኛ ትምህርት፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን በኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል በመካሄድ ላይ ነው።
ጅማ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከ57 በላይ የግል እና የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተëማት በኮንቬንሽኑ ላይ ተሳታፊ ናቸው። ጅማ ዩኒቨርሲቲም የሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲሁም የፈጠራ ስራዎችን ይዞ በክብር ታድሟል።
የእለቱ የክብር እንግዳ የኢፌድሪ ፕሬዝደንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኮንቬንሽኑን በከፈቱበት ወቅት በአውደ-ርዕዩ በተመለከቷቸው የፈጠራ ውጤቶች መደሠታቸውን ገልፀው፤ ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ፣ ለሳይንስ እና ለጥበብ ፈርቀዳጅ ነች ብለዋል።
ክብርት ፕሬዝደንቷ አክለውም የአክሱም ሀውልት፣ የጅማ አባጅፋር ቤተመንግስት፣ የጎንደር ፋሲለደስ፣ የጀጎል ግምብ፣ እና የህክምና ቅመማ የቆዩ የሀገራችን የሳይንስ ጥበብ መሆናቸውን አውስተዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው ኮንቬንሽኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቁዋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር እውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት ያለመ እንደሆነ ገልፀዋል።
መዳረሻውን ሁለንተናዊ ብልፅግና ያደረገው ይህ ኮንቬንሽን አዋጭ የሆኑ አስተሳሰቦችን ለግብርና፣ ለምርምር እና ለቴክኖሎጂ እድገት ለማዋል እየተሰራ እንደሆነም ክቡር ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንደተናገሩት የዛሬው ፕሮግራም ዋነኛ አላማ የመጀመሪያውን የሳይንስ ሽልማት ይፋ ማድረግ እንደሆነና የምርምር ስራዎችን እየተወዳደሩ በየዓመቱ የሚሸለሙበት መሆኑን ገልፀዋል።
ኮንቬንሽኑ የሀገሪቱን ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ምሁራን እና ቴክኖሎጂስቶችን ከኢንዱስትሪ ጋር በማገናኘቱ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፤ከዚሁ ጋር ተያይዞም፣ የሳይንስ፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን (HEART Convention 2021) በዛሬው እለት የተመሰረተ ሲሆን በየዓመቱ የሚቀጥል እንደሆነ ተነግሯል።
በተቅዋማት የተሠሩ የምርምር፣ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማሳያ አውደ-ርዕይ በተለያዩ አዝናኝ ትዕይንቶች ታጅቦ በመካሄድ ላይ ነው።
የሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅ፣ በስራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ እና በተቅዋማት መካከል ምቹ ሁኔታና ትስስር መፍጠርን ዓላማው ያደረገው ኮንቬንሽን ለአራት ቀናት የሚቆይ ነው።