ከፍተኛ ትምህርትን መልሶ ስለማስጀመር

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያደርገውን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ከፍተኛ ትምህርትን መልሶ ለማስጀመር በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተቋቋመው የምልከታ ኮሚቴ ገለጸ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ 11 ኮሚቴዎችን በማቋቋም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ለመቀበል ምን ዝግጅት አድርገዋል በሚል ወቅታዊ አቋምን በመፈተሸ ላይ ይገኛል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ላለፉት ሰባት ወራት ተቋማቱ ከገፅ ለገፅ ትምህርት አሰጣጥ ርቀዉ መቆየታቸዉ የሚታወቅ ሲሆን ኮሚቴዉም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተከላከለ ትምህርት ማስቀጠል የሚችልበትን ቅድመ ዝግጅት ቀደም ሲል በተቀመጠዉና 70 ቅድመ ሁኔታዎችን ከያዘ መመዘኛ አንፃር በዉይይት፣ በምልከታ እና በሰነድ ፍተሻ ሲገመግም ቆይቶ ዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ኮሚቴዉ በሁለት ቀናት የምልከታ ቆይታዉ ከሰዉ ሃይል አደረጃጀት፣ የመሰረተ-ልማትን ከማሟላት እና ሌሎች ዝግጅቶች አንፃር በዩኒቨርሲቲዉ ዋናዉ ግቢ እና ሶስቱም ካምፓሶች ቅኘት አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ኮምፒዉተራይዝድ የሆነ የእቅድና ሰነድ አያያዝ፣ የተማሪዎች ሬጅስትራር ሲስተም፣ የማናጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም፣ ኦንላይን ቤተ-መፅሀፍት፣ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት (6238) የኮቪድ-19 ጥቆማ መስጫ፣ የለይቶ ማቆያዎች ዝግጅት፣ የህክምና ክትትል መስጫ ስፍራ፣ የግንዛቤ መፍጠሪያ ፕሮግራሞችና በሽታዉን የመከላከል ዘመቻዎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዉ የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ዩኒቨርሲቲዉ ዉጤታማ የሆነባቸዉ እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ በሌሎች ተቋማትም ሊስፋፉ የሚገባቸዉ ምርጥ ተሞክሮዎች ስለመሆናቸዉ ገምጋሚ ኮሚቴዉ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኮምዩኒኬሽን ስርዓት የተሻለ አፈፃፀም የታየበት ስለመሆኑ የምልከታ ኮሚቴዉ ገልጿል፡፡
ኮሚቴዉ በጅምር ያሉ ስራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፆ፤ የተማሪዎች የመታወቂያ ካርድ የቆዩ በመሆናቸዉ ቅያሪ እንዲደረግ፣ በመማሪያና መኝታ ቦታዎች በቂ በሴንሰርና መካኒካል ስርዓት የሚሰሩ የመታጠቢያ ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ አሰራሮችን ከህግ ጋር በማይጣረስ መልኩ ማዘመን፣ የአለም ጤና ድርጅት እና የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሰቀመጣቸዉን አቅጣጫዎች መሰረት ያደረና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን መፍጠር በስፋት ሊሰራባቸዉ ይገባል ብሏል፡፡
ተማሪዎች ከትምህርት ርቀዉ በመቆየታቸዉ እና የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱም ከዚህ ቀደም ከነበረዉ ሂደት ለየት ባለ መልኩ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ዩኒቨርሲቲዉ እንደ ሶሻል ወርክና ሳይኮሎጂ ትምህርት ባለሙያዎችን በማስተባበር ለተማሪዎች ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግ እንዲሁም የኮቪድ-19 ተጠቂዎችን የሚያክሙ የጤና ባለሙያዎች ተማሪዎችን ከበሽታዉ ለመከላከል የሚረዱ ተግባራትን እንደሚያከናዉኑ የዩኒቨርሲቲዉ አመራር አካላት ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዉ በዝግጅት ሂደት ላይ አብዛኞቹን ቅድመ-ሁኔታዎች ያሟላና በማሟላት ሂደት ላይ በመሆኑ፤ መልካም ስራዎቹን በማስቀጠል መሻሻል የሚገባቸዉን በማሻሻል ዝግጁነቱን ይበልጥ እንደሚያጠናክር ለምልከታ ኮሚቴዉ አረጋግጧል፡፡