እጅ ለእጅ ስንያያዝ ይበልጥ እንደምቃለን! ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘደንት

የኮቪድ – 19 ምላሽ የፈጠራ ስራዎች ዓውደ-ርዕይ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ጉባኤ አስተባባሪዎች የእውቅና እና ምስጋና ፕሮግራም በሃጫሉ ሁንዴሳ ሲቪክ ማዕከል ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ በዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት በሀገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገባቸው ስኬቶች በየደረጃው የሚገኙ ሰራተኞቹ ጥረትና ያልተቆጠበ አስተዋፅዎ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

አንድ ተቋም ያለሰራተኞቹ ትጋትና ንቁ ተሳትፎ ራዕይና ግቦቹን ማሳካት እንደማይችል እሙን ሲሆን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ይህንን በተግባር እያሳዩ መሆናቸዉ ተነግሯል፡፡

የዩኒቨርሲቲዉ ሰራተኞች ያበረከቱት አስተዋፅዎ ጉልህ በመሆኑና አስቸጋሪ ኃላፊነቶችን ከፍ ባለ የጥራት ደረጃ ለመወጣት በመቻሉ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዉ ከፍ ብሎ እንዲታይ፤ ማንኛም ኃላፊነት ቢሰጠው በብቃት ማጠናቀቅ የሚችል የሀገር ሀብትና የልማት አለኝታ እንደሆነ በእጅጉ አስመስክራችኋልና ለዚህም ታላቅ ምስጋናና ክብር ይገባችኋል ሲሉ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ አሞካሽተዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ጉባኤና አዉደ-ርዕዩን በበላይነት ሲመሩ ለነበሩ የተለያዩ ኮሚቴዎች አስተባባሪዎችና አባላት በመድረኩ የእዉቅና ሰርተፊኬት የተበረከተላቸዉ ሲሆን በስራዉ ለተሳተፉት ሁሉ በየስራ ክፍላቸዉ አማካኝነት ተመሳሳይ የእዉቅና ሰርተፊኬቶች እየተሰጣቸዉም ይገኛል፡፡

ይህንን የመተባበርና ተጋግዞ የመስራት ባህልን ማስቀጠልና ዩኒቨርሲቲውን ወደላቀ ከፍታ ማድረስ የሁሉም ሃላፊነት በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት በላቀ ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የዕውቅናና ምስጋና ዝግጅቱ በዩኒቨርሲቲው መዝናኛ ክበብ እራት ግበረዣ እና በሸነን ጊቤ የሙዚቃ ባንድ ጣዕመ ዜማዎች የታጀበ ነበር ፡፡

በዝግጅቱም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ፣ የሴኔትና ካውንስል አባላት እና የአካዳሚክና የአስተዳድር ሰራተኞች እንዲሁም ጉባኤውና ዓውደ-ርዕዩ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የጸጥታና ደህንነት፣ ባህልና ቱሪዝም፣ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ነበሩ፡፡