አገልግሎት ሰጪ የስራ ክፍሎች በእቅዳቸዉ ዉስጥ አካል ጉዳተኝነትን ታሳቢ ማድረግ ይገባቸዋል ተባለ፡፡

ጅማ ዩኒቨርሲቲ መጋቢት 21/2013ዓ.ም
*****************************************
አገልግሎት ሰጪ የስራ ክፍሎች በእቅዳቸዉ ዉስጥ አካል ጉዳተኝነትን ታሳቢ ማድረግ ይገባቸዋል ተባለ፡፡
ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የነበረዉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የስራ ክፍሎች ሃላፊዎች ስልጠና ተጠናቋል፡፡
ስልጠናዉ ስለ አካል ጉዳተኝነት ግንዛቤ ለመፍጠር እና በተለያዩ የስራ ሂደቶች ዉስጥ አካታችነትን ለማጎልበት ያለመ ነዉ፡፡
ለስራ ሃላፊዎቹ ስልጠናዉን ሲሰጡ የነበሩት ዶ/ር ተክሉ ገመቹ እንዳሉት ስልጠናዉ አመራሩ አካል ጉዳተኞችን መረዳት እና ፍላጎታቸዉ ምን እንደሆነ እንዲለዩ እንዲሁም የሚገባቸዉን አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
በአካል ጉዳተኝነት ላይ ሰዎች የተሳሳተ ግንዛቤ ነዉ ያላቸዉ ያሉት ዶ/ር ተክሉ ይህም አንድም ባለማወቅ ሁለትም ሆን ተብሎ ሊሆን ስለሚችል ስለ አካል ጉዳተኝነት በብዙ ጎኑ በስልጠናዉ ለማሳየት እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡
እንደ እሳቸዉ ገለፃ አካል ጉዳተኝነት ማለት አንድ ሰዉ በአካሉ ላይ ጉዳት መኖሩ ብቻ ሳይሆን በጉዳቱ ምክንያት ምን አይነት ችግሮች አጋጠሙት የሚሉት በአንድ ላይ ሲመጡ ነዉ፡፡
ህብረተሰባችን ከቃላት አጠቃቀም ጀምሮ በጥንቃቄና አካል ጉዳተኞችን ምቾት በማይነሳ መልኩ በመጠቀም ተግባቦትን ሊፈጥር እንደሚገባ በስልጠናዉ ላይ ተነስቷል፡፡
በአካል ጉዳተኝነት ላይ የወጡ አለም አቀፍ ህጎችን ጨምሮ ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ተያይዘዉ ለአመራር አካላቱ የቀረበ ሲሆን ከዚህ ስልጠና በኋላ በስራቸዉ ዉስጥ አካተዉ እንደሚሰሩ ይጠበቃል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ አቃፊ እና ሁሉን ያካተተ እንዲሆን ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡