በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አገልግሎት ስር የሚገኙ የተለያዩ የስራ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ፡፡
ዉይይቱ የ2013ዓ.ም የተማሪዎች ቅበላን አስመልክቶ ሊደረጉ ስለሚገባቸዉ ጥንቃቄዎች ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ታዉቋል፡፡
የጥበቃና ደህንነት፣ የጠቅላላ አገልግሎት፣ የተማሪዎች መኝታ ተቆጣጣሪዎች፣ የተማሪዎች ካፍቴሪያ እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች፤ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዉ ሲመጡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ከግምት ዉስጥ ያስገባ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ለመፍጠር በተደረገዉ ዉይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በዉይይቱ ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ እንደተናገሩት ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል እንደከዚህ በፊቱ ባለዉ ሂደት መቀጠል ባለመቻሉ የሚመለከተዉ የስራ ክፍል ሁሉ ከዚህ ቀደም ከነበረዉ ዝግጅት በተለየ ሁኔታ መዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚደንቱ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እራሳችንን እየተከላከልን ሰላማዊ እና ምቹ የመማር ማስተማር ሂደትን ለመፍጠር ተባብረን እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርቲ ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡