በአረንጓዴ አሻራችን 70,000 ሺህ የቡና ችግኞችን ጨምሮ 270,000 ልዩ ልዩ ችግኖች ለተከላ ተዘጋጅተዋል

በአረንጓዴ አሻራችን 70,000 ሺህ የቡና ችግኞችን ጨምሮ 270,000 ልዩ ልዩ ችግኖች ለተከላ ተዘጋጅተዋል
ሰኔ 19/2013 ዓ.ም
*********************************
አረንጓዴ አሻራ ቀጣይነት ላለዉ መማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎት፤ እንዲሁም ገቢ ማመንጫ በሚል ሀሳብ ችግኞችና የፍራፍሬ ተክሎችን እንተክላለን፤ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፡፡
በግብርናና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ስር በሚገኘዉ ኢላዳሌ እርሻ ጣቢያ የጅማ ዩኒቨርሲቲ አረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ተካሂዷል፡፡
መርሀ-ግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ “ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት” ጥሪ አካል እንደሆነ ተገልፀዋል፡፡
በመርሀ-ግብሩ ላይ በዩኒቨርሲቲዉ የሁሉም ኮሌጆች እና ኢንስቲትዩቶች ሰራተኞች ተገኝተዉ አሻራቸዉን አኑረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዉ የግብርናና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፍቃዱ ምትኩ አሻራቸዉን ባስቀመጡበት ወቅት የዛሬዉ መርሀ-ግብር ዓላማ ከምርምር፣ መማር ማስተማር እና ማህበረሰብ አገልግሎትን ቀጣይነት ከማረጋገጥ ባለፈ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸዉን ገቢ በማመንጨት እራሳቸዉን እንዲችሉ ለማድረግ እየተሰራ በመሆኑ እንደ ገቢ ማመንጫነትም ያገለግላል ተብሏል፡፡
ዛሬ የተተከሉት የቡና ችግኞች ፍሬ አፍርተዉ የዩኒቨርሲቲዉን ስም ብራንድ በማድረግ ለገበያ እንደሚቀርቡም ተነግሯል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት በኢላዳሌ እርሻ ጣቢያ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ ላይ ተገኝተዉ አሻራቸዉን ባኖሩበት ወቅት በመርሀ-ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲዉ የምርምርና የሳይንስ መፍለቂያ እንደመሆኑ ችግኞችን ስንተክል በሳይንሳዊ መንገድ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ዓመታትም መርሀ-ግብሩ የአየር ንብረት ለዉጥን በመከላከል የአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ሚዛንን ለመጠበቅ እንዲያስችል በተለይም በጊቤ ተፋሰስ ውስጥ ባሉ ሁለት አዋሳኝ ወረዳዎች ውስጥ የግልገል ጊቤ ግድብን ከደለል ለመከላከል አፈር መሸርሸርን ለመከላከል ሲሰራ ነበር ብለዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብ በየአመቱ የተለያዩ መርሆችን ይዞ የሚቀጥል በመሆኑ በዚህ አመት ፍራፍሬዎችን እና ቡናን ጨምሮ ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ሊሰጡ የሚችሉ በአጠቃላይ 270,000 የችግኝ ዓይነቶች ለተከላ የተዘጋጁ መሆኑንና ከነዚህ ውስጥም 70,000 የቡና ችግኞች መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡
በዛሬው የማስጀመሪያ መርሃ-ግብርም 25 ሺህ የቡና ችግኞችን ለመትከል በተዘጋጀው የኢላዳሌ ጣብያ ወደ 800 በሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው ማ/ሰብ አባላት ተከላው የተካሄደ ሲሆን፤ የተከልነዉን የመንከባከብና የመጠበቅ ስራም የኛዉ በመሆኑ ሁላችንም በሀላፊነት ልንሰራ ይገባል ተብሏል፡፡
የዛሬዉ መርሀ-ግብር የመዝናኛ፣ የገቢ ማመንጫ፣ የኢኮ-ቱሪዝምና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን ለማሳካት ዘርፈ-ብዙ ሚና እንዳለዉ ተነግሯል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብሩ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለሚቀጥሉት ሰባት ሳምንታት የሚቀጥል ነዉ ተብሏል፡፡
May be an image of one or more people, people standing, tree and outdoors