በስኬት ጎዳና

በስኬት ጎዳና
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 19/2013ዓ.ም
***************************************
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች በአዉሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም (EU-IOM) ምርጥ ተብለዋል፡፡
ይህ የተባለዉ በአዳማ ከተማ በአዉሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጥበቃ እና መልሶ ማቋቋም የጋራ ጥምረት (EU-IOM joint initiative for migrant protection and reintegration) ለሁለት ቀናት በተካሄደዉ ወርክሾፕ ላይ ነዉ፡፡
በወርክሾፑ ላይ በተለያዩ ተቋማት እየተተገበሩ ያሉ በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት ስራዎች የቀረቡ ሲሆን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶች አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከስደት ተመላሽ የሆኑ ዜጎችን በማደራጀት በፍየል፣ አሳ፣ ዶሮ እርባታ እና በእንስሳት መኖ ማቀነባበር የእዉቀት፣ የሙያ፣ የክህሎት፣ የገንዘብ እና የክትትል ድጋፎችን በማድረግ በርካታ ዉጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
የተቀናጀ የኣሳ እና ዶሮ እርባታ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አህመድ ሰዒድ የወርክሾፑ ተሳታፊዎች ላነሷቸዉ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዉ እያከናወናቸዉ የሚገኙ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በምርጥ ተሞክሮነት የተወሰዱ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ሊተገበሩ የሚገባቸዉ መሆኑ በወርክሾፑ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ተስፋዬ ገበየሁ በወርክሾፑ እንዳሉት የመሰል ፕሮጀክቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በተጠቃሚዎች አመለካከትና ግንዛቤ ላይ ሳይንሳዊ ምርምር በማድረግ አትሞ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡
ም/ፕሬዚደንቱ አክለዉም እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ቀጣይነት ኖሯቸዉ የሚፈለገዉን ዉጤት እንዲያመጡ ዩኒቨርሲቲዉ አስፈላጊዉን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ቀጣይነት ባለዉ ሁኔታ እየተተገበሩ በመሆናቸዉና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጥቅም ስለሚያስገኙ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እያከናወናቸዉ የሚገኙ የማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶች ለማስፋፋት ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
በወርክሾፑ ተሳታፊ የነበሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና (EU-IOM) በአዉሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ ፕሮጀክት ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡
ተቋማቱ ከዩኒቨርሲቲዉ ጋር ያላቸዉን ተስስር ለማጠናከር እንደሚፈልጉም ገልፀዋል፡፡