ስቴም [STEM] ማዕከል ምረቃ
ሚያዝያ 08/ 2013 ዓም
****************************
ጅማ ዩኒቨርስቲና ስቴም-ፓውር [STEM Power] በጋራ ያደራጁት የሳይንስ ትምህርቶች ቤተ-ሙከራና ልህቀት ማዕከል በዛሬው ዕለት ተመረቀ፡፡
ስቴም [STEM] ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስናና ሂሳብ ትምህርቶችን ማዕከል አድርጎ ቤተ-ሙከራውን ያደራጀ ማዕከል ሲሆን፣ ለመጪው ትውልድ ከንድፈ-ሀሳብ ባሻገር ያለውን የተግባር ትምህርት በልጅነታቸው እንዲታጠቁና እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው፡፡
ከምርቃቱ ስነ-ሥርዓት በፊት በዩኒቨርሲቲው ሴኔት በተደረገው ውይይት፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳነት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ባደረጉት ንግግር ዛሬ ለምርቃት የበቃው ማዕከል፣ በጅማ ዞንና አካባቢው ለሚገኙ ተማሪዎች የላቀ የቴክኒዮሎጂ መፍለቂያና የኢኖቬሽን አገልግሎት መስጫ ዓይነተኛ ተቋም ይሆናል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የስቴም ፖወር ዋና ዳይርክተር ወይዘሪት ቅድስት ገብረአምላክ በበኩላቸው፣ የተፈጥሮ ሣይንስ ትምህርት ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ብቻ ሳይሆን፣ ለማህበራዊ ህይወት ለውጥም መሰረት ነው ብለዋል፡፡
ውይይቱን በጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና አሳታፊነት ዳይርከተር ዶ/ር ጉዲና ተረፈ እና የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፐሬዝደንት ዶ/ር ተስፋዬ ገበየሁ የመሩት ሲሆን፣ ማዕከሉ ስራውን እንዴት እንደሚሰራና የሚያመጣውን ለውጥ፣ እንዲሁም ቀጣይነቱን በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተካሂድዋል ፡፡
የማዕከሉን ምረቃ ተከትሎ በተከናወነው ጉብኝት፣ ማዕከሉ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ የተደራጀ ቢሆንም፣ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ትምህርት የሚሰጥባቸው ደረጃቸውን የጠበቁ የምህንድስና ትምህርት መርጃ መሳሪያዎች፣ ኮምፒዩተሮችና የ3-ዲ ዲጂታል ማተሚያ መሳሪያዎች የተሟላለት ነው፡፡
በውይይቱና ምርቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ፣ ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የኢንስቲትዩት ተወካዮችና ልዩ ልዩ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሀላፊዎች ተገኝተዋል