ማስክ አፕ ጅማ

ጅማ ዩኒቨርሲቲ መጋቢት 23/2013ዓ.ም
*****************************************
ሁሉንም ማሽን ላይ ማስቀመጥ አንችልም፤ ራሳቸዉን እንዲጠብቁ ማድረግ እንጂ፡ ዶ/ር አብዱሰመድ ሁሴን የጅማ ድንገተኛ አደጋ ክወና ማዕከል የሪስክ ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ፡፡
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም ዘመቻ (Mask up Campaign) በጅማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የኮቪድ-19 በሽታ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በጅማ ከተማም በተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንዳለ ይነገራል፡፡
ዘመቻዉን ያስጀመሩት የጅማ ድንገተኛ አደጋ ክወና ማዕከል የሪስክ ኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ቡድን መሪ ዶ/ር አብዱሰመድ ሁሴን በከተማዋ የኮቪድ-19 በሽታ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደመጣ ገልፀዉ ሁሉንም ታማሚዎች በመተንፈሻ ማሽን መርዳት አንችልም፤ የመጨረሻዉ የህክምና ደረጃ ራስን መጠበቅና የኮቪድ-19 ፕሮቶኮሎችን በአግባቡ መተግበር ነዉ ብለዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር እና አቃቤ ህግ የወጣዉን መመሪያ የሚመለከታቸዉ አስፈፃሚ አካላት በአግባቡ በመተርጎም ማህበረሰቡን ከኮቪድ-19 በሽታ እንዲታደጉ ዶ/ር አብዱሰመድ ሁሴን ጥሪያቸዉን አቅርበዋል፡፡
በ2012ዓ.ም በጅማ ዞን የመጀመሪያዉ የኮቪድ-19 ኬዝ ከተገኘ ግዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አንድ ሺህ አንድ መቶ ዘጠና ሶስት ሰዎች በበሽታዉ ተይዘዋል፡፡
ከነዚህም መካከል ዘጠኝ መቶ ሃያ ሶስቱ አገግመዉ ወደ ቤታቸዉ የተመለሱ ሲሆን ሰላሳ ስምንት ሰዎች ደግሞ በበሽታዉ ምክንያት ህይወታቸዉ አልፏል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ሃያ ስምንት ሰዎች በኮቪድ-19 የተያዙ ሲሆን አስራ ስድስቱ በፅኑ ህመም ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡
የጅማ ከተማ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ሂንዲያ በማስክ-አፕ ዘመቻ ላይ እንደተናገሩት ኮቪድ-19 እንደ ሀገር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነዉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተገናኘ የኦክሲጂን ተጠቃሚዎች ቁጥርም እጅጉን ጨምሯል፡፡
ወ/ሮ ሂንዲያ ሙሀመድ በንግግራቸዉ የኮቪድ-19 በሽታ እያደረሰ ያለዉን ጉዳት ለመቀነስ ማህበረሰቡ ከመቼዉም ግዜ በላቀ መልኩ ራሱን እንዲጠብቅ እና ማስክ በአግባቡ እንዲጠቀም ብለዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ አራቱም ካምፓሶች፣ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት፣ እንዲሁም አጂፕ፣ መናኸሪያ፣ አዌቱ፣ ፈረንጅ አራዳ፣ ሸንን ጊቤ፣ ለገሃር እና መርካቶ ዘመቻዉ የተከናወነባቸዉ የጅማ ከተማ አካባቢዎች ናቸዉ፡፡