ለሶስት ቀናት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተካሔደው ዓዉደ-ርዕይ እና የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ

የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠናን ለማስቀጠልና ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ዓልሞ ሲመክር የነበረው መድረክ ተጠናቋል፡፡ የምክክር መድረኩ ገንቢ የሆኑ ግብዓቶች የተሰበሰቡበት፣ የከፍተኛ ትምህርትን ለማስቀጠል መሰረት የተጣለበትና በባለድርሻ አካላት የጋራ መግባባት የተፈጠረበት ነበር፡፡

ከዚሁ የውይይት መድረክ ጎን ለጎን በተካሔደውና 45 ዩኒቨርሲቲዎችና ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በተሳተፉበት ዓዉደ-ርዕይ ላይ በቀረቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች በቂ ልምድ የተወሰደባቸዉና በሀገር ዉስጥና በዉጪ ለገበያ ሊቀርቡ የሚችሉ እንደሆኑ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

በምሽቱም የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ የተለያዩ ሁነቶች ተከናውነዋል፡፡ በዚሁም ዝግጅት ላይ የጅማ ሰርከስ ቡድን የተለያዩ ትዕይንቶችን እና ሙዚቃዎችን ያቀረበ ሲሆን የጅማና የአካባቢውን ባህል የሚገልፁ ስጦታዎች ለኮንፍራንሱ ተሳታፊዎች ተበርክተዋል፡፡

በዝግጅቱ ማጠቃለያ ላይ አጭር የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት እምዬ ቢተው እንደገለጹት ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በተቀናጀ መልኩ ይህንን ታላቅ የውይይትና የዓውደ ርዕይ መድረክ በማዘጋጀቱ ታላቅ ምስጋና ሊቸረው ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ የዩኒቨርሲቲው አመራር አባላት፣ ዝግጅቱን ለማከናወን የተቋቋሙ ኮሚቴ አባላት፣ የጸጥታ አካላት እና የጅማ ከተማና ዞን አስተዳደር እና አጠቃላይ ነዋሪዎችን አመስግነዋል፡፡

——–
ክቡር ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዲኤታዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንቶች እና ጥሪ የተደረገላችሁ አካላት የዩኒቨርሲቲያችን እንግዶች በመሆናችሁ ታላቅ ክብር ተሰምቶናል፡፡ ወደፊትም ዩኒቨርሲቲያችን ተመሳሳይ መድረኮችን የማዘጋጀት ሙሉ ፍላጎት ያለዉ መሆኑን ስንገልፅላችሁ በታላቅ ደስታ ነዉ፡፡

ጅማ ዩኒቨርሲቲ