ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ልዩ ፍላጎት ላላቸዉ ተማሪዎች

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚገባቸዉ ተነገረ፡፡
ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉን ጅማ ዩኒቨርሲቲ አስታዉቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፣ የ ECDD ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲሴቢሊቲ ዴቨሎፕመንት ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ተክሌ፣ የ ECDD ቦርድ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሴኔት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት አዳራሽ በተከናወነዉ የምክክር መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የዉይይት መነሻ ጽሁፎች በጅማ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ፍላጎት ትምህር ክፍል እና ECDD የቀረበ ሲሆን ከተሳታፊዎች ጋር ተመክሮበታል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናዉን መቆየቱ ተገልፅዋል፡፡
ልዩ ፍላጎት የሚሹ ተማሪዎች በቆይታቸዉ ምቹ ግዜ እንዲኖራቸዉና ዉጤታማ ሆነዉ እንዲወጡ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ፍላጎት የሚሹ ተማሪዎች መጠቀሚያ ማዕከልን ማቋቃሙ ተነግሯል፡፡
ዩኒቨርሲቲዉ በቀጣይም አካታች፣ አሳታፊ እና እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የተገለፀ ሲሆን ለዚህም ስኬት በዩኒቨርሲቲዉ ያሉ የተለያዩ የስራ ክፍሎች በዉይይት መድረኩ መሳተፋቸዉ ታዉቋል፡፡