ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ2012 የትምህርት ዘመን ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁ 1 ሺህ 409 ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቨርቹዋል አስመረቀ፡፡

የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፣ የጅማ ከተማ ከንቲባና የዩኒቨርሲቲዉ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ክቡር አቶ ቲጃኒ ናስር እና የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ክቡር አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ በእንግድነት ተገኝተዋል፡፡
የእለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የእለቱ ተመራቂዎችንና ቤተሰቦቻቸዉን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዉ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለሀገራችን ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ መሆኑንና በተለይም በጤናዉ ዘርፍ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ በበኩላቸዉ ዩኒቨርሲቲዉ በመጭው ጊዜ ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅና ቴክኖሎጂን ለትምህርት ግብዓት እንደዋና መሣሪያ መጠቀም አስፈላጊና ወሳኝ በመሆኑ ዩኒቨርስቲያችን ያሉትን የትምህርት ፕሮግራሞች በቴክኖሎጂ የታገዙና ከዘመኑ ጋር የሚጣጣሙ እንዲሆኑ ለማስቻል በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዉ ለዚህም በOnline የሚደገፉ የቴክኖሎጂ ትምህርቶችን መተግበር መጀመራችን አይነተኛ ምሳሌ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ወንድ 423 ሴት 116 በድምሩ 539 በድህረ ምረቃ መርሃ ግብሮች በማስተርስ ዲግሪ፤ በስፔሻሊቲ ሰርቲፊኬት እና በፒኤችዲ ዲግሪ ወንድ 616 ሴት 254 በድምሩ 870 በአጠቃላይ 1ሺህ409 ተማሪዎችን በዛሬው ቀን አስመርቋል፡፡ ከነዚህም መካከል 2ቱን በCeramic Engineering ፒኤችዲ ፕሮግራም ለመጀመሪያ ግዜ አስመርቋል፡፡